አምባሳደር ይበልጣል አዕምሮ በሱዳን የኢጋድ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ጋር ተወያዩ

ሚያዝያ 12/2013 (ዋልታ) – በሱዳን የኢትዮጵያ አምባሳደር ይበልጣል አዕምሮ በሱዳን የኢጋድ ጽህፈት ቤት ዋና ኃላፊ ሚኒስትር ኦስማን ሃሰን ቢላል ጋር በቀጠናዊ የጋራ ጉዳዮች ዙሪያ ተወያይተዋል፡፡

በውይይቱም አምባሳደር ይበልጣል በኢትዮጵያና ሱዳን ድንበር ጉዳይ እና በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ድርድር ሂደት የኢትዮጵያን አቋም በዝርዝር አስረድተዋል፡፡

በዚህም በሁለቱም ጉዳዮች ያሉ ውዝግቦች በሠላማዊ መንገድና በድርድር እንዲፈቱና በቀጠናው ሰላምና ደህነነት እንዲረጋገጥ ኢትዮጵያ ቁርጠኛ መሆኗን ገልጸዋል፡፡

አምባሳደሩ በቀጠናው ሰላም መስፈን ኢጋድ የሚጫወተው ገንቢ ሚና ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመው፣ ለዚህም ኢትዮጵያ ያላት ድጋፍ ጠንካራ ነው ብለዋል፡፡

ሚኒስትር ኦስማን ሃሰን ቢላል በበኩላቸው፣ ኢጋድ በድንበሩና በሕዳሴ ግድብ ዙሪያ ያሉ ልዩነቶችን በቅርበት እየተከታተለ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል።

አክለውም በድርጅቱ አባላት መካከል የሚከሰቱ ልዩነቶችን በሠላማዊ መንገድና በድርድር ይፈቱ ዘንድ ኢጋድ አዎንታዊ ሚና ለመጫወት ያለውን ዝግጁነት መግለጻቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ አመላክቷል፡፡