በኬንያ በተካሄደው የ5 ሺሕ ሜትር ውድድር ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በሁለቱም ጾታዎች አሸነፉ


ሚያዝያ 13/2016 (አዲስ ዋልታ) ትላንት ማምሻውን በኬኒያ በተካሄደው የዓለም አትሌቲክስ ኮንቲኔንታል ቱር ጎልድ ውድድር በ5 ሺሕ ሜትር በሁለቱም ጾታዎች ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች አሸንፈዋል።

በሴቶች የ5 ሺሕ ሜትር ውድድር አትሌት ማርታ አለማየው ርቀቱን 15 ደቂቃ ከ14 ሰከንድ ከ54 ማይክሮ ሰከንድ በሆነ ሰዓት በአንደኝነት ስትጨርስ፣ ለምለም ንብረት 15 ደቂቃ ከ20 ሰከንድ ከ99 ማይክሮ ሰከንድ በሆነ ሰዓት ውድድሩን በመጨረስ 3ኛ ሆና አጠናቃለች። ሌላዋ አትሌት ሽቶ ጉሚ ውድድሩን በአራተኝነት አጠናቃለች።

በሌላ በኩል በወንዶች የ5 ሺሕ ሜትር ውድድር አብዲሳ ፈፍሳ ርቀቱን 13 ደቂቃ ከ34 ሰከንድ ከ77 ማይክሮ ሰከንድ በሆነ ሰዓት በማጠናቀቅ አሸናፊ መሆኑን ከኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።