ኢትዮጵያ ወደ ታዳሽ ኃይል እያደረገችው ያለን ሽግግር መልከ ብዙ ጠቀሜታ እንዳለው የዓለም አቀፍ ታዳሽ ኃይል ዋና ዳይሬክተር ገለጹ

ሚያዚያ 13/2016 (አዲስ ዋልታ) ኢትዮጵያ ወደ ታዳሽ ኃይል አጠቃቀም ለመሸጋገር የምታደርገው ሽግግር መልከ ብዙ ጠቀሜታ እንዳለው የዓለም አቀፍ ታዳሽ ኃይል ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ራውል አልፋሮ ፔሊኮ ገልፀዋል።

ዋና ዳይሬክተሩ በ14ኛው የዓለም አቀፍ ታዳሽ ኃይል አጀንሲ ጉባኤ መዝጊያ ላይ ባደረጉት ንግግር የታዳሽ ኃይል ፕሮጀክቶች ኢንቨስትመንትን ፋይናንስ በማድረግ ረገድ አዋጭ እንዲሆኑ የአተያይ ለውጥ ለማድረግ አስፈላጊ ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ እያደረገች እንዳለችው በኃይል ዘርፍ የግል-የመንግስት ትብብርን ማጠናከር እና የትብብር ጥረቶችን በማፋጠን ዓለም አቀፍ ለውጥ ማምጣት ይገባል ብለዋል።

በታዳሽ ኃይል ዘርፍ የሚደረገው ሽግግር በሶስት እጥፍ የስራ እድል እንደሚፈጥርና በአሁኑ ወቅት 13 ነጥብ 7 ሚሊዮን የስራ ዕድልን በፈረንጆቹ 2050 ወደ 40 ሚሊየን እንደሚያሳድገው ነው ዋና ዳይሬክተሩ የጠቀሱት።

ከኃይል ጋር በተያያዙ ቴክኖሎጂዎች ላይም የሚካሄደው ኢንቨስትመንት ለስራ ፈጠራ ምቹ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር) በበኩላቸው በታዳሽ ኃይል ዘርፍ በኩል መተማመን እንዲጨምር የሚያደርግ የግል-የመንግስት ትብብር ሞዴል መዘጋጀቱን ጠቅሰዋል።

ኢትዮጵያ የግሉ ዘርፍ ኢንቨስትመንትን በማሳደግ በፀሀይ፣ በንፋስ እና በጂኦተርማል ፕሮጀክቶች ላይ የፋይናንስ ምንጭ አቅምን ለማሳደግ እርምጃዎችን እየወሰደች ሲሆን እ.ኤ.አ. በ 2030 ኢኮኖሚያችንን ወደ ፊት ለማራመድ እና በኃይል ራስን ለመቻል 100% የታዳሽ ኃይል እቅዳችንን ለማሳካት ተቃርበናል ብለዋል።

በመድረኩ ለታዳሽ ኃይል ፕሮጀክቶች አስተማማኝ የፋይናንስ ምንጭ ጉዳይ፣ የአፍሪካ የኃይል ሽግግር፣ የጅኦተርማልና የአረንጓዴ ሀይድሮጅን ሚና፣ የአፍሪካን የኃይል ሽግግር ለማፋጠን አስፈላጊ ፖሊሲዎችና ክህሎቶችን የተመለከቱ ጉዳዮች መነሳታቸውን ከውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል።