በሐሰተኛ ትርክት የተፈጠረውን ሃሳብ በማረም ለሀገራዊ አንድነት አስተዋጽኦ ለማድረግ ሥራዎች ሲሰሩ ቆይተዋል – ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ

መጋቢት 13/2016 (አዲስ ዋልታ) በክልሉ በሐሰተኛ ትርክት የተፈጠረውን ሃሳብ በማረም ለሀገራዊ አንድነት አስተዋጽኦ ለማድረግ ሥራዎች ሲሠሩ መቆየታቸውን የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ ገለጹ።

ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ ከሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የሥራ ኃላፊዎች ጋር እየመከሩ ነው።

በምክክሩ የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ይርጋ ሲሳይ፣ የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር መስፍን አርዓያ (ፕ/ር)፣ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽነሮች እና ምሁራን ተገኝተዋል።

ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ የምክክር ኮሚሽኑ ተግባር በክልሉ በምን መልኩ እየተከናወነ እንደሆነ፣ በቀጣይስ ምን ዓይነት አቅጣጫ መቀመጥ አለበት በሚለው ጉዳይ ላይ ይመከራል ነው ያሉት።

ለአሁን ብቻ ሳይሆን መጻዒ እድል የሚወስኑ ጥያቄዎች ያሉበት ክልል እና ሀገር መሆኑንም ተናግረዋል።

በሐሰተኛ ትርክት የተፈጠረውን ሃሳብ በማረም ለሀገራዊ አንድነት አስተዋጽኦ ለማድረግ ሥራዎች ሲሠሩ መቆየታቸውን ገልጸው በክልሉ የተፈጠረው የፀጥታ ችግር በሚፈለገው ፍጥነት ልክ ሳይሠራ መቆየቱንም አመላክተዋል።

አሁን ላይ ክልሉ በተሻለ የሰላም እንቅስቃሴ ላይ መሆኑንም ገልጸው የኮሚሽኑ ተግባራት በአግባቡ እንዲፈጸም የራሳችንን አስተዋጽኦ ማበርከት ይገባናል ነው ያሉት።

የኮሚሽኑ ዓላማ እና ግብ አንድነቷ የተጠበቀ ኢትዮጵያን ለመፍጠር መሆኑንም አንስተዋል።

የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር መስፍን አርዓያ (ፕ/ር) ኮሚሽኑ ኢትዮጵያዊያንን ወደ ግጭት የከተተውን እና የማያግባባውን ችግር አጀንዳ በመቅረጽ እና ምክክር በማድረግ ወደ መግባባት ላይ ለመድረስ ነው ብለዋል።

የኮሚሽኑ የመጀመሪያ ሥራ የሀገሪቱን ሁሉንም አካባቢዎች ማዳረስ እና ችግሮችን መለየት መሆኑንም ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ በሚገኙ ወረዳዎች ላይ ለመድረስ ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር በጋራ መሥራታቸውን መግለጻቸውንም አሚኮ ዘግቧል።

ከፍተኛ አለመግባባቶች ባሉባት ሀገር በአጭር ጊዜ ውስጥ ሥራን መቋጨት እንደማይቻልም ተናግረዋል።

የሃይማኖት ተቋማት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ሴቶች፣ የአካል ጉዳተኞች፣ ወጣቶች እና ሌሎች የማኅበረሰብ ክፍሎች ባለድርሻ አካላት መሆናቸውንም ገልጸዋል።