በክልሉ ግብርናውን ለማዘመን 17 መርኃ ግብሮች እየተተገበሩ ነው – ርዕስ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ

ግንቦት 26/2014 (ዋልታ) ግብርናውን ለማዘመን 17 መርኃ ግብሮች ተመርጠው እየተተገበሩ መሆኑን የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ ገለፁ።
በኦሮሚያ ክልል ርዕስ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ፣ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ ሎሚ በዶ እንዲሁም በምክር ቤቱ የመንግሥት ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጅጌ የተመራ የምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴ አመራሮችና አባላትን ያቀፈ ልኡካን ለመጪው ክረምት የአረንጓዴ አሻራ ፕሮግራም እየተዘጋጀ ያለውን የችግኝ ጣቢያዎችን ጎብኝተዋል።
ከአረንጓዴ አሻራው ፕሮግራም የዝግጅት ቦታ ጉብኝት በፊት በሞጆ ለወጪ ምርት ታስቦ እየተዘጋጀ ያለውን የአቮካዶ ችግኝ ጉብኝት ተከናውኗል።
በጉብኝቱ ርዕስ መስተዳድር ሽመልስ የክልሉን ግብርና ለማዘመንና ከመሰረቱ ለመለወጥ ሰፊ ጥናቶች ተካሂደውና ወደ 17 የሚሆኑ መርኃ ግብሮች ተመርጠው እየተሰሩባቸው መሆኑን ተናግረዋል።
ከነዚህ ውስጥ ዘጠኙ ተቀርፀው እየተተገበሩ መሆናቸውን የተናገሩት ርዕስ መስተዳድሩ በአሁኑ ወቅት 1 ነጥብ 3 ቢሊዮን የቡና ችግኝ በክላስተር ለማልማት የዝግጅት ሥራ እየተጠናቀቀ መሆኑን አንስተዋል።
በአጠቃላይ በቡና ኢንሼቲቩ ባለፉት ሶስት ዓመታት ከ2 ነጥብ 9 ቢሊዮን በላይ የቡና ችግኞች የተተከሉ ሲሆን በተመሳሳይ የሻይ ልማት ላይ በምዕራብ ኦሮሚያ ሁሉም ዞኖች ላይ እየተሰራ መሆኑን ለአብነት አንስተዋል።
በአሁኑ ወቅት 17 ሺሕ የውሃ መሳቢያ ሞተሮች ለአርሶ አደሩና አርብቶ አደሩ መሰራጨቱን ጠቅሰው በቀጣይ 20 ሺሕ የውሃ መሳቢያ ሞተሮችን ለማሰራጨት መታቀዱንም አክለዋል።
በዘንድሮው ዓመት ከ600 ሺሕ ሄክተር በላይ ስንዴን በመስኖ ማልማት መቻሉን የገለፁ ሲሆን በመጪው የበጀት ዓመት ከ1 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት በመስኖ ስንዴ ለማልማት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም አመልክተዋል።
ርዕስ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ የቢራ ገብስ ልማት በክልሉ በስፋት በመከናወኑ ከውጭ ይገባ የነበረውን የቢራ ብቅል በሀገር ውስጥ የገብስ ምርት መተካት መቻሉንና ይህም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።
የቡና፣ የሻይ፣ የሙዝ፣ የማር ልማት፣ የገጠር ፋይናንስ አገልግሎት፣ የደን ልማት፣ የአቮካዶ፣ የእርሻ ሜካናይዜሽን እና ሌሎችም የግብርና ተግባራት በቴክኖሎጂ መደገፍ ከተቀረፁት ኢንሼቲቮች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው።
የምግብ ዋስትና ማረጋገጥ፣ ገቢ ምርቶችን በሀገር ውስጥ መተካት፣ የሥራ ዕድል ፈጠራና ምርቶችን በብዛት፣ በጥራትና በፍጥነት ማምረት ዋነኞቹ ግቦች እንደሆኑም ነው የተናገሩት።
ለመጪው ክረምት ከ4 ነጥብ 6 ቢሊዮን በላይ ለተለያየ አገልግሎት የሚውሉ ችግኞችን ለመትከል እስከ አሁን ከ2 ነጥብ 3 ቢሊዮን የጓድጓድ ዝግጅት መጠናቀቁንም ገልጸዋል ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው።
በዋናነት የግብርና ዘርፉን ከመሰረቱ ለመለወጥ በሚደረገው በዚህ ጥረት ታዲያ የምክር ቤቱ ዕገዛ፣ ክትትልና ድጋፍ ካልታከለበት የተፈለገውን ውጤት ማምጣት እንደማይቻል ነው የገለጹት።