በክልሉ ግንባታቸው ባልተጠናቀቁ ማደያዎች በህገወጥ መንገድ የተከማቸ ነዳጅ ተያዘ

ሰኔ 29/2014 (ዋልታ) በአማራ ክልል እንጅባራ ከተማ አስተዳደርና ሰሜን ሜጫ ወረዳ ግንባታቸው ባልተጠናቀቁ ማደያዎች በህገ-ወጥ መንገድ የተከማቸ ነዳጅ መያዙን የክልሉ ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ አስታወቀ።

በቢሮው የንግድ ውድድርና ሸማቾች ጥበቃ መሠረታዊ ዕቃዎች ጉዳይ ዳይሬክተር ታፈረ ይመር ለኢዜአ እንደገለጹት ነዳጁ ሊያዝ የቻለው ከቢሮው፣ ከዞን፣ ከወረዳዎችና ከተማ አስተዳደሮች በተዋቀረ ቡድን በተደረገ ክትትል ነው።

በእንጅባራ ከተማ አስተዳደር በተደረገ ክትትል ግንባታው ባልተጠናቀቀ ማደያ 184 ሺሕ ሊትር ነዳጅ መገኘቱን ገልጸው ከነዳጁ ውስጥ 46 ሺሕ ሊትር የሚሆነው ቤንዚን ሲሆን ቀሪው ናፍጣ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በተመሳሳይ በምዕራብ ጎጃም ዞን ሰሜን ሜጫ ወረዳ ልዩ ቦታው ጉንጫ ተብሎ በሚጠራ ስፍራ በአራት ቦቴ የተገለበጠ ነዳጅ በህገ ወጥ መንገድ ተከማችቶ መገኘቱን አመልክተዋል።

በሁለቱም ቦታዎች ተደብቆ የተገኘው ነዳጅ በአንድ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት የቀረበና ግንባታቸው ባልተጠናቀቁ ሁለት ማደያዎች እንደተገኘ አብራርተዋል።

“ማደያዎቹ ከክልል ጀምሮ ከዞን፣ ከወረዳና ከከተማ አስተዳደር ከተሰጣቸው የግንባታ ፈቃድ ውጭ ገና ህጋዊ ዕውቅና ያላገኙና የማጠራቀሚያ ታንከር ብቻ የተቀበረባቸው መስፈርቱን ያላሟሉ ናቸው” ብለዋል።

ነዳጁ የስርጭት አግባቡን ያልተከተለ፣ ባልተጠናቀቀ ማደያ ያለዕውቅና የተከማቸና ለአደጋ በሚያጋልጥ መልኩ የተቀመጠ መሆኑን አስረድተዋል።

“ድርጊቱ በመንግሥት ድጎማ የመጣን ነዳጅ ህጋዊ ባልሆነ መንገድ አከማችተው አግባብ ያልሆነ ትርፍ ለማግኘት የተደረገ በመሆኑ ተጠያቂ ያደርጋቸዋል” ብለዋል።

እንደ ዳይሬክተሩ ገለፃ ቢሮው እስካሁን ህገወጥነት ላይ በተሳተፉ 22 ነዳጅ ማደያዎች ላይ ከጽሑፍ ማስጠንቀቂያ እስከ ማሸግ የደረሰ ርምጃ ወስዷል።

“ገና ለገና የነዳጅ ዋጋ ይጨምራል በሚል የንግድ ህጉን በጣሰ መንገድ ተከማችቶ የተገኘ ነው” ያሉት ደግሞ የአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ ኃላፊ ፀሐይነህ ቦጋለ ናቸው።

“የነዳጅ ህገወጥነትን ከወረዳዎች ጋር በመቀናጀት በተደረገ ቁጥጥር የማሸግና የማስጠንቀቂያ እርምጃ መውሰድ ጀምረናል” ብለዋል።

በድብቅ የተገኘው ነዳጅ በህግ ቁጥጥር ስር ውሎ በንግድ አዋጁ መሠረት በፍትህ አካላት አስተማሪ ውሳኔ እንዲያገኝ እንደሚደረግ አመልክተዋል።

በአቋራጭ ለመክበር የሚፈልጉ በዘርፉ የተሰማሩ አካላት ከድርጊታቸው ተቆጥበው ሐምሌ 1 ቀን 2014 ዓም ተግባራዊ የሚደረገው የታለመለት የነዳጅ ማሻሻያ ስኬታማ እንዲሆን የድርሻውን እንዲወጡ ኃላፊው አሳስበዋል።

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW