አየርላንድ ከአፍሪካ ጋር ያላትን ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት ለማጠናከር እንደምትፈልግ ገለጸች

ሰኔ 29/2014 (ዋልታ) አየርላንዳዊያን የንግዱ ማኅበረሰብ በአፍሪካ ያላቸውን ኢንቨስትመንት ይበልጥ ማሳደግ እንደሚፈልጉ ባሳለፍነው ሳምንት በደብሊን በተካሄደው 7ኛው የአፍሪካ አየርላንድ የኢኮኖሚ ፎረም ላይ አስታውቀዋል፡፡

በፎረሙ ላይ ንግግር ያደረጉት የአፍሪካ ልማት ባንክ ፕሬዝዳንት አኪንውሚ አዴሲ (ፒኤችዲ)ና በአፍሪካ ኢንቨስት ካላደረጋችሁ በንግድ ውስጥ የላችሁም ብለዋል።

ከሁለት ዓመት በፊት የአየርላንድ ቀጥታ የውጭ ኢንቨስትመንት በአፍሪካ 572 ሚሊዮን ዶላር ወይም ከሀገሪቱ አጠቃላይ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ከአንድ በመቶ በታች መሆኑን የባንኩ ፕሬዝዳንት ተናግረዋል፡፡

ቁጥሩ እጅግ በጣም አነስተኛ መሆኑን አስረድተው የአየርላንድ ባለሀብቶች በአፍሪካ በተለያዩ የኢንቨስትመንት አማራጮች ላይ ለመሰማራት ይበልጥ መስራት እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡

የአየርላንድ የውጭ ጉዳይ እና የመከላከያ ሚኒስትር ሲሞን ኮቬኔይ በበኩላቸው አገራቸው ከአፍሪካ ጋር ያላትን የኢኮኖሚ ትስስር ማጠናከር እንደምትፈልግ ገልጸው እ.አ.አ በ2025 በአፍሪካ እና በአየርላንድ መካከል ያለው የኢኮኖሚ ትስስር አምስት ቢሊየን ዩሮ ለማድረስ ይሰራል ብለዋል፡፡

ከአፍሪካ ልማት ባንክን ፕሬዝዳንት ጋር የተወያዩት የአየርላንድ ፕሬዝዳንት ማይከል ዲ ሂግንስ ሀገራቸው ከአፍሪካ ጋር በኢኮኖሚው ዘርፍ ትስስር ለመፍጠር የረጅም ግዜ ፍላጎት እንዳላት አመልክተዋል።

አየርላንድ የአፍሪካ ልማት ባንክን የልማት ፈንድ የተቀላቀለች ሲሆን ለባንኩ የአየር ንብረትን መላመድ የሚችል ግብርና ለተሰኘው ፕሮጀክት ሁለት ሚሊዮን ዩሮ ድጋፍ ማድረጓን ባንኩን ጠቅሶ ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW