በክልሉ 1 ሺህ 432 ምርጫ ጣቢያዎች ለምዝገባ ክፍት ተደርገው አገልግሎት እየሰጡ መሆናቸው ተገለጸ

አቶ ጣሃ አሊ

ሚያዝያ 12/2013 (ዋልታ) – በአፋር ክልል 1 ሺህ 432 ምርጫ ጣቢያዎች ለምዝገባ ክፍት ተደርገው አገልግሎት እየሰጡ መሆናቸው ተገለጸ፡፡

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ የአፋር ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጣሃ አሊ ለዋልታ በስልክ እንደገለጹት፣ በምርጫ ሂደቱ በተለይ ለሴቶች እና ወጣቶች እንዲመቻቸው ለማድረግ በቅርብ ርቀት በተዘጋጁ የምዝገባ ቦታዎች በንቃት እየተሳተፉ ይገኛሉ፡፡

ክልሉ ሞቃታማ በመሆኑ ለማህበረሰቡ የሚመች ስዓትን በመምረጥ የምዝገባ ሂደቱ እየተከናወነ መሆኑን የጠቆሙት ኃላፊው፣ እስካሁን ከ171 ሺህ በላይ መራጮች የምዝገባ ካርድ መውሰዳቸውን አስታውቀዋል፡፡

ለአፋር ክልል በትራንስፖርት ችግር የምርጫ ቁሳቁስ ከሁለት ሳምንታት በኋላ በመድረሳቸው ምክንያት የምዝገባ ሂደቱ የተጓተተ ቢሆንም፤ ከምርጫ ቦርድ ጋር በመነጋገር ተጨማሪ ቀናቶች እንዲፈቀዱልን እንጠይቃለን ብለዋል፡፡

በክልሉ የሲቪክ ማህበራት ምርጫ ላይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ እየሰሩ የነበረ ቢሆንም፤ በሚያጋጥማቸው የፋይናንስ እጥረት ምክንያት ስራዎች መቀዛቀዛቸውን ነው አቶ ጣሃ የገለጹት፡፡

በክልል እና በዞን ደረጃ የተዋቀረ ኮሚቴ በማዘጋጀት እና ከተለያዩ ድጋፍ ሰጭ አካላት ጋር በመተባበር በቀጣይ በሀገራዊ ምርጫ ዙሪያ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ እንደሚሰራም ተናግረዋል፡፡

የምርጫ ሂደቱን ፍትሐዊ እና ነጻ ለማድረግ በክልሉ አምስት ዞኖች የካቤኔ ከፍተኛ አመራር ኮሚቴ ተዋቅሮ እየተሰራ ነው ያሉት ኃላፊው፣ በዚህም በቅርበት ሂደቱ ላይ ትኩረት በማድረግ በየሰዓቱ ሪፖርት በማቅረብ እና በክልል ደረጃ በተቋቋመው የምርጫ አስፈጻሚ ኮሚቴ ግምገማ በማድረግ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በሀገሪቱ በሁሉም ከልሎች የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን መራጮች በተቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት የምርጫ ካርዳቸውን በመውሰድ ሀገራዊ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡም አቶ ጣሃ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

(በብርሃኑ አበራ)