አቶ ደመቀ መኮንን ከአውሮፓ ህብረት የስጋት አስተዳደር ኮሚሽነር ጋር ተወያዩ

አቶ ደመቀ መኮንን

ሚያዝያ 12/2013 (ዋልታ) – የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የአውሮፓ ህብረት የስጋት አስተዳደር ኮሚሽነር ያኔዝ ሌናርቺችን ዛሬ በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።

በውይይታቸው በትግራይ ክልል እየተደረገ ያለው የመልሶ ማቋቋም ጥረት የሚደነቅ እንደሆነ ገልጸው፣ የሚታዩ ችግሮችን በመፍታት የሰብዓዊ ድጋፍ አቅርቦቱ መጠናከር እንዳለበት አንስተዋል።

ኮሚሽነር ሌናርቺች እየተሻሻለ የመጣውን ተደራሽነት በማድነቅ ተደራሽ መሆን ያልቻሉ ሩቅ የገጠር አካባቢዎችን ለመድረስ የተጠናከረ ስራ መሰራት እንዳለበት ጠቅሰዋል።

በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽንና በተባበሩት መንግስት ድርጅት (ተመድ) ተቀናጅተው በክልሉ ተፈጽሟል የተባለውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት ተቀናጅተው እንዲያጣሩ ከስምምነት ላይ መደረሱን አዎንታዊ ርምጃ መሆኑን ገልጸዋል።

የኤርትራ ሰራዊት እንዲወጣ መወሰኑን ያደነቁት፣ ኮሚሽነር ሌናርቺች ሂደቱ መፋጠን እንደሚገባ  አስምረውበታል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በበኩላቸው መንግስት ክልሉን መልሶ ለማቋቋም ከፍተኛ ጥረት ማድረጉን ገልፀው፣ በርካታ ለውጦች መመዝገባቸውም አንስተዋል፡፡

“በክልሉ የተስተዋሉ ችግሮችን ለማቃለል ሌሎች አካላትም መንግስት በሚሰራቸው ስራዎች አላስፈላጊ ትችቶችን ከመሰንዘር ይልቅ አስፈላጊ ድጋፍ ቢደረግ ስራው በአጭር ጊዜ ውጤታማ መሆን ይችላል” ብለዋል፡፡

የሰብዓዊ ድጋፍ አጋሮች የመገናኛ መሳሪያ የማግኘት ሁኔታን በተመለከተ ባለው መመሪያ መሰረት ተፈጻሚ እንደሚሆን ጠቁመዋል።

ውይይቱ ላይ የተገኙት የብሔራዊ የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር ምትኩ ካሳ በበኩላቸው፣ በርካታ የሰብአዊ ድጋፍ አጋሮች በአብዛኛው በመቀሌ ከተማና አቅራቢያዋ እንደሚንቀሳቀሱ ጠቁመዋል።

እስካሁን ከተደረገው የ4 ነጥብ 5 በመቶ ሶዎች የሰብዓዊ ድጋፍ ውስጥ አጋሮች የሸፈኑት ምግብ ነክ ካልሆነው ሰባት በመቶ፣ ምግብ ነክ ደግሞ 30 በመቶ ያህሉን እንደሆነ ጠቅሰዋል።

በዚህ ረገድ አሁንም በክልሉ የተጎዱ ሰዎችን በማገዝ ረገድ ዋነኛው ተዋናይ መንግሥት በመሆኑ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ሰብዓዊ ድጋፍን ያጠናክራል ተብሎ ይጠበቃል ብለዋል፡፡

በዚህ ረገድ አሁንም በክልሉ የተጎዱ ሰዎችን በማገዝ ረገድ ዋነኛው ተዋናይ መንግሥት በመሆኑ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ሰብዓዊ ድጋፍን ያጠናክራል ተብሎ ይጠበቃል ብለዋል፡፡

ካለፉት 15 ቀናት ጀምሮ በክልሉ ያሉትን አካባቢዎች ተደራሽነት በማስፋት ለሰብዓዊ ድጋፍ ተደራሽ ያልሆኑ ስድስት ወረዳዎች አሁን በወታደራዊ አጃቢ ተደራሽ ሆነዋል ማለታቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡