በክልሎቹ የሀገራዊ ምክክር ተሳታፊዎች ልየታ በትኩረት እየተሰራበት መሆኑ ተነገረ

መጋቢት 27/2016 (አዲስ ዋልታ) በአማራ እና በትግራይ ክልል ለሀገራዊ ምክክሩ የተሳታፊዎች ልየታ የማጠናቀቅ ሂድት በትኩረት እየተሰራበት መሆኑን የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አስታወቀ።

ኮሚሽኑ ዛሬ በሰጠው መግለጫ ከ1 ሺሕ 300 በላይ ወረዳዎችና የከተማ አስተዳደሮች ላይ የተሳታፊዎች ልየታ የስራ ማከናወኑን የኮሚሽኑ ቃል አቀባይ ጥበቡ ታደሰ ተናግረዋል።

ቃል አቀባዩ አክለውም በአማራ ክልል ያለው የጸጥታ ችግር ሀገራዊ ምክክሩ ላይ የሚሳተፉ አካላትን የመለየት ስራን እያዘገየባቸው መሆኑን ገልጸዋል።

ነገር ግን በክልሉ ያሉ ምሁራንን፣ የዩኒቨርሲቲ መምህራንን እና ተባባሪ አካላትን በመለየት ስልጠና መሰጠቱን ነው ቃል አቀባዩ የጠቆሙት።

በትግራይ ክልልም የተሳታፊ አካላትን ልየታ ለመጀመር የክልሉን ጊዜያዊ አስተዳደር ምላሽ እየጠበቁ መሆኑን ተናግረዋል።

በኦሮሚያ ክልል በጅማ እና በወለጋ ተወካዮችን የመምረጥ ሂደቱ የተጠናቀቀ ሲሆን ከ70 በላይ ወረዳዎች ላይም ስራዎች እየተጠናቀቁ መሆናቸውን አስታውቀዋል።

በአሁኑ ወቅትም ከህዝባዊ መድረኮች የአጀንዳ ግብአቶችን የማሰባሰብ ሂደቱን ለማስጀመር ቅድመ ዝግጅት ተጠናቋል ተብሏል።

በሄለን ታደሰ