ወደ ሀገር ለሚገቡ 2ኛ ትውልድ ኢትዮጵያውያን በቦሌ አየር ማረፊያ አቀባበል እየተደረገ ነው

የቱሪዝም ሚኒስትሯ አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ

መጋቢት 27/2016 (አዲስ ዋልታ) በሁለተኛ ዙር ወደ ሀገር ለሚገቡ 2ኛ ትውልድ ኢትዮጵያውያን በቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ አቀባበል እየተደረገላቸው ይገኛል።

በአቀባበል ስነ – ስርዓቱ ላይ የቱሪዝም ሚትስትሯ አምባሳደር ናሲሴ ጫሌ እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ብርቱካን አያኖን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

ሁለተኛው ምዕራፍ ኢትዮጵያውያን የእረፍት ጊዜያቸውን ተጠቅመው የሀገራቸውን ታሪክ እንዲያውቁ፣ የአያቶቻቸውንና ቅድመ አያቶቻቸውን አይበገሬነትና መስዋዕትነት እንዲሁም ለጥቁር ህዝቦች ነፃነት ያበረከቱትን አስተዋፅዖ አንዲረዱ ለማድረግ ዓላማ እንዳለው ተጠቅሷል።

በዚህ አኩሪ የአያትና ቅድመ አያቶቻቸው ታሪክ ተነሳስተው በዘመናቸው የሀገር ፍቅራቸው እንዲዳብርና ፍሬያማ አስተዋፅዖ እንዲያበረክቱ ለማስቻል የታቀደ መሆኑ በመረጃው ተገልጿል::

“ታሪካዊ መሰረትዎን ይወቁ” በሚል ለሚካሄደው ሁለተኛው ምዕራፍ መርኃ ግብር የኢትዮጵያ አየር መንገድ የበረራ ትኬት፣ ሆቴሎች፣ አስጎብኚ ድርጅቶች የዋጋ ቅናሽ በማድረግ 2ኛ ትውልድ ኢትዮጵያውያኑን ተቀብለው እያስተናገዱ እንደሚገኙ ከቱሪዝም ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያሳያል።

“ባክ ቱ ዩር ኦሪጅን” የሚል ስያሜ የተሰጠው እና ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በውጭ ለሚኖሩ የ2ኛ ትውልድ ኢትዮጵያውያን ያቀረቡት ጥሪ በሶስት ዙሮች የሚካሄድ ነው::

በዚህም ከታህሳስ 20 እስከ ጥር 30 በመጀመሪያው ዙር ከብዝኃ ባህል መሰረትዎ ጋር ይገናኙ በሚል በተሰየመው መርኃ ግብር ወደ ሀገራቸው ገብተው እንደነበር ይታወሳል።