በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ክፉኛ የተጎዳችው ብራዚል ክትባት መስጠት ጀመረች።
የብራዚል ጤና ቁጥጥር መሥሪያ ቤት ሁለት የኮሮናቫይረስ መከላከያ ክትባቶች ለዜጎቹ እንዲሰጡ ካፀደቀ በኋላ የመጀመሪያውን ክትባት አንዲት ነርስ መከተቧ ተገልጿል፡፡
የብራዚሉ ጤና ቁጥጥር ባለሥልጣን እውቅና የሰጣቸው ክትባቶች የኦክስፎርዱ አስትራዜኔካ እና የቻይናው ሲኖቫክ ክትባቶች ናቸው። እነዚህ ሁለቱ ክትባት በብራዚል 27 ግዛቶች በሙሉ ተሰራጭተዋል ተብሏል።
ክትባቱን የወሰደችው የ54 ዓመቷ ነርስ ሞኒካ ካላዛንስ የምትባል ስትሆን፣ የሳኦ ፖሎ ነዋሪ መሆኗ ተገልጿል።
ብራዚል የኮሮናቫይረስ ክትባትን መስጠት የጀመረችው ከአህጉሩ አገራት በሙሉ ዘግይታ ነው።
በብራዚል የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በተከሰተበት ወቅት የሚያደርሰውን ጉዳት ያጣጥሉ የነበሩት የአገሪቱ ፕሬዝዳንት ዣየር ቦልሶናሮ፣ አገራቸው በሁለተኛ ዙር የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ስትጠቃ ዳግም ተቺዎቻቸው እያብጠለጠሏቸው ይገኛሉ።
እሁድ ዕለት ብቻ 551 ሰዎች በወረርሽኙ ሰበብ መሞታቸው የተመዘገበ ሲሆን፣ ከስድስት ቀን ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ የሟቾች ቁጥር ከ1000 በታች የተመዘገበበት ዕለት ነውም ተብሏል።
በብራዚል የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ከተከሰተበት ጊዜ አንስቶ 209 ሺህ ሰዎች በቫይረሱ ምክንያት ሲሞቱ፣ ይህም ከአሜሪካ በመቀጠል በዓለም ላይ ሁለተኛ ሆኖ ተመዝግቧል።
በአገሪቱ 8.4 ሚሊየን ሰዎች በኮሮናቫይረስ መያዛቸው በምርመራ ሲታወቅ ይህም በዓለም ላይ ሦስተኛዋ አገር ያደርጋታል።
የጤና ሚኒስትሩ ኤድዋርዶ ፓዙኤሎ በአገራቸው የሚሰጠው የኮሮናቫይረስ መከላከያ ክትባት፣ ክትባቱን በአገር ውስጥ እንዲያመርቱ ፈቃድ በተሰጣቸው ሁለት የመድኃኒት አምራች ኩባንያዎች ይታገዛል ማለታቸውን ቢቢሲ ዘግቧል።