በወፍ ዋሻ ደን የተከሰተው የእሳት አደጋ ከአቅም በላይ መሆኑ ተገለጸ

መጋቢት 16/2013 (ዋልታ) – በሰሜን ሸዋ ዞን በአንኮበር ወረዳ በወፍ ዋሻ የተፈጥሮ ጥብቅ ደን የተከሰተው የእሳት አደጋ ከአቅም በላይ መሆኑ ተገለጿል።

በወፍዋሻ የተፈጥሮ ጥብቅ ደን በተከሰተው የእሳት ቃጠሎ እሰካሁን በ150 ሄክታር በላይ የተፈጥሮ ሀብት ውድመት መድረሱን የወረዳው መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

የጽህፈት ቤቱ ሀላፊ አቶ ዓባይ ታደሰ ለኢዜአ እንደገለጹት የዛሬ አራት ቀን በደን ክልሉ የተከሰተውን የእሳት ቃጠሎ ለማጥፋት ማህበረሰቡን ያሳተፈ እንቅስቃሴ ቢካሄድም እስካሁን በቁጥጥር ስር ማዋል አልተቻለም።

አደጋው ከተከሰተ ጀምሮ በየቀኑ እስከ 700 የማህበረሰብ ክፍሎችን በማሳተፍ ለመቆጣጠር ጥረት ቢያደርጉም ከቃጠሎው መስፋት ጋር ተያይዞ እንዳልተቻለ ተናግረዋል።

በተለይም በጥብቅ ስፍራው ውስጥ እንደ ዝግባ፣ ወይራ፣ ጥቁር እንጨትና ሌሎች  ሀገር በቀል የሆኑ እድሜ ጠገብ ዛፎች መገኛ በመሆኑ ቃጠሎውን በቀላሉ ለመቆጣጠር አስቸጋሪ እንዳደረገው ገልጸዋል።

በተጨማሪም የአካባቢው መልካዓ ምድር አቀማመጥ ገደላማ በመሆኑ የመቆጣጠር ስራውን አዳጋች ያደረገው መሆኑን አቶ አባይ አመልክተዋል።

“በጥብቅ ደኑ ውስጥ በኢትዮጵያ ብቻ የምትገኘው የሶረኔ ወፍን ጨምሮ የነብር፣ ሰሳ፣ ጭላዳ ዝንጀሮና ሌሎች ብርቅየ እንስሳት ላይ ጉዳት እንዳይደርስ ስጋት ፈጥሯል” ብለዋል።

የችግሩን ስፋት በማስገንዘብ የአጎራባች ወረዳዎችና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላትን ትብብር ለማግኘት ጥሪ መቅረቡን አስታውቀዋል።

በተመሳሳይ  በመንዝ ጓሳ ማህበረሰብ አቀፍ ፓርክ በተመሳሳይ ቀን ተከስቶ የነበረው የእሳት ቃጠሎ ዘጠኝ ሄክታር መሬት ላይ የሚገኝ ደን ማውደሙን  የገለጹት ደግሞ በመንዝ ጌራ ምድር ወረዳ መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም ጽህፈት ቤት ሀላፊ አቶ ግርማየ አሰፋ ናቸው።

ከአንድ ሺህ በላይ የሚሆኑ የአካባቢው አርሶ አደሮችና ሌሎች ነዋሪዎችን በማሳተፍ አሁን ላይ ቃጠሎው በቁጥጥር ስር መዋሉን ተናግረዋል።

የእሳት አደጋው ዳግም ተከስቶ በፓርኩ በሚገኙ ቀይ ቀበሮ፣ ሰሳ፣ ነብር፣ ሚዳቆዎችና ሌሎች አእዋፍና አጥቢ እስሳት ላይ ጉዳት እንዳይደርስ ጥብቅ ክትትል እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

በወፍ ዋሻና በመንዝ ጓሳ ፓርክ ቃጠሎ በአካባቢዎቹ አርሶ አደሮች ማሳ ላይ የሚደረግ የቁጥቋጦ ማቃጠል ስራ መንስኤ ሊሆን የሚችሉ አመላካች መረጃዎች እየወጡ መሆኑን ሀላፊዎቹ አስታውቀዋል።