በዓለ-ሲመቱ በሰላም መጠናቀቁን የፀጥታ የጋራ ግብርኃይል አስታወቀ

መስከረም 25/2014 (ዋልታ) ኢትዮጵያ ወደ አዲስ ምዕራፍ የምትሸጋገርበት የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የትናንቱ በዓለ ሲመት በሰላም መጠናቀቁን የፀጥታ የጋራ ግብርኃይል አስታወቀ፡፡

በመስቀል አደባባይ የተከናወነው ሥነ-ሥርዓት በሰላም እንዲጠናቀቅ የከተማችን ነዋሪዎች ላሳዩት ጨዋነት ለተሞላበት ቀና ትብብር ግብርኃይሉ ምስጋናውን አቅርቧል፡፡

መስከረም 24 ቀን 2014 ዓ.ም ኢትዮጵያ በአዲስ መንግስት፣ በአዲስ ተስፋ አዲስ ምዕራፍ የምትጀምርበት ቀን ነው።

የጋራ ግብርኃይሉ ከፌዴራል ፖሊስ፣ ከብሔራዊ መረጃ ደህንነት፣ ከመከላከያ ሰራዊትና ከሌሎች የፀጥታ አካላት ጋር አስቀድሞ ዕቅድ በማውጣት እና ህብረተሰቡን በማስተባበር የተከናወኑት ተግባራት ውጤት አስገኝተዋልም ብሏል፡፡

ሥነ-ሥርዓቱ በሰላም ተጀምሮ እንዲጠናቀቅም በፍፁም ሙያዊ ብቃት ኃላፊነታቸውን የተወጡ ለመላው የፀጥታ አካላትና ለሰላም ወዳዱ የከተማችን ነዋሪዎች የፀጥታ የጋራ ግብርኃይል ከፍ ያለ ምስጋናውን በታላቅ አክብሮት ያቀርባል ብሏል በመግለጫው፡፡