ሐምሌ 04/2013 (ዋልታ) – በዘንድሮው ምርጫ ህዝቡ የጣለበትን ሃላፊነትና አደራ ከሁላችን በሁላችን ለሁላችን በሚል መርህ ፍጹም አካታችና አሳታፊ በሆነ መልኩ በብቃት እየተወጣ የኢትዮጵያን ብልጽግና ለማረጋገጥ ተግቶ እንደሚሰራ የብልጽግና ፓርቲ ገለጸ፡፡
ሐምሌ 3 ቀን 2013 ዓ.ም የተገለጸውን የመጀመሪያ ደረጃ የምርጫ ውጤት አስመልክቶ ብልጽግና ፓርቲ መልዕክት አስተላልፏል።
ሀምሌ 3 ቀን 2013 ዓ.ም የተገለጸውን የመጀመሪያ ደረጃ የምርጫ ውጤት አስመልክቶ ከብልጽግና ፓርቲ የተላለፈ መልዕክት።
ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም የተካሄደው አገራዊ ምርጫ በእርግጥም የኢትዮጵያን አሸናፊነት ያረጋገጠና ለአገራችንም የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ጠንካራ መሰረት የጣለ ምርጫ ነበር ማለት ይቻላል።
እኛ ኢትዮጵያዊያን የውስጥ ፖለቲካዊ ጉዳዮቻችንን በራሳችን የምንፈታና ለዚህም በራሳችን አቅም ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ በማድረግ የሰለጠነ የፖለቲካ ባህልና ጠንካራ የዴሞክራሲ ሥርዓት መገንባት መጀመራችንን በዘንድሮው አገራዊ ምርጫ ማሳየት ችለናል።
በዚህ ምርጫ በእርግጥም ኢትዮጵያ አሸንፋለች። መላው ኢትዮጵያዊያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች እንኳን ደስ አላችሁ። የዘንድሮው ምርጫ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ በርካታ ባለድርሻ አካላት የማይተካ ጉልህ ሚና ተጫውተዋል።
በተለይ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድን ጨምሮ ሁሉም የዴሞክራሲ ተቋማት በምርጫው ሂደት ነጻና ገለልተኛ ሆነው ያከናወኗቸው ተግባራት ባለፉት ዓመታት የተካሄዱት የተቋማት ሪፎርም እርምጃዎች መልካም ፍሬ ማፍራት መጀመራቸውን የሚያምላክቱ ተጨባጭ ማሳያዎች ናቸው፡፡
በቅድመ ምርጫ፣ በምርጫ እለትና በድህረ ምርጫ ወቅቶች ደከመን ሰለቸን ሳትሉ የተጣለባችሁን ሃላፊነት በብቃት ለተወጣችሁ ተቋማት በሙሉ ላቅ ያለ ምስጋና ልናቀርብ እንወዳለን።
የአገራችን ፖለቲካዊ ችግር የሚፈታው ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ በማከናወንና እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት በመገንባት ብቻ መሆኑን በማመን በዘንድሮው ምርጫ በንቃት ለተሳተፋችሁ ፓርቲዎችና የግል ተወዳዳሪዎች ለኢትዮጵያ ማሸነፍ ትልቅ አስተዋጽዖ አበርክታችኋልና ያለን አክብሮትና የላቀ ምስጋና ይድረሳችሁ።
የዘንድሮው ምርጫ የኢትዮጵያ ህዝብ ከፍታ ጎልቶ የወጣበት መሆኑ በአለም አደባባይ ታይቷል።
ምርጫው በሰላም ተጀምሮ እንዲጠናቀቅ ብቻ ሳይሆን ዴሞክራሲና የህዝብ ፍላጎት አሸንፎ እንዲወጣ ኢትዮጵያዊያን በቅድመ ምርጫው፣ በምርጫው እለትና በድህረ ምርጫው ለአሁኑም ሆነ ለቀጣዩ ትውልድ ተሞክሮ የሚሆን ታሪካዊ ሚና ተጫውታችኋልና ልዩ ምስጋና ይገባችኋል። ኢትዮጵያዊያን ሁላችንም አሸንፈናልና እንኳን ደስ አላችሁ።
ብልጽግና ፓርቲ በዘንድሮው ምርጫ ህዝቡ የጣለበትን ሃላፊነትና አደራ ከሁላችን በሁላችን ለሁላችን በሚል መርህ ፍጹም አካታችና አሳታፊ በሆነ መልኩ በብቃት እየተወጣ የኢትዮጵያን ብልጽግና ለማረጋገጥ ተግቶ የሚሰራ መሆኑን ልናረጋግጥላችሁ እንወዳለን።
ኢትዮጵያ አሸንፋለች!