በደቡብ ወሎ እና ማዕከላዊ ጎንደር ዞኖች ከ500 በላይ ተጠርጣሪዎች ተያዙ

ግንቦት 18/2014 (ዋልታ) በአማራ ክልል ደቡብ ወሎ እና ማዕከላዊ ጎንደር ዞኖች “በሕግ ማስከበር ዘመቻው” ከ500 በላይ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የዞኖቹ አስተዳዳሪዎች ገለጹ።

በደቡብ ወሎ ዞን “ሕግ ማስከበር ዘመቻው” በተለያዩ ወንጀሎች የተጠረጠሩ 422 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ውለው ጉዳያቸው በሕግ እየታየ እንደሚገኝ የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አብዱ ሁሴን ገልጸዋል።

ግለሰቦቹ በነፍስ ግድያ፣ ስርቆት፣ ሽብር፣ ከማረሚያ ቤት የጠፉ፣ በሕገ-ወጥ ገንዘብና ጦር መሳሪያ ዝውውርና በሌሎች ወንጀሎች የተጠረጠሩ መሆናቸውን አመልክተዋል።

ብሔርና እምነትን ሽፋን አድርገው የተጀመረውን ዘመቻው ለማደናቀፍና ለአሸባሪው ሕወሓት መረጃና ገንዘብ ሊያቀብሉ የነበሩ ግለሰቦችን ከአጎራባች ክልሎችና ዞኖች በመቀናጀት እንዲያዙ ተደርጓል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

በተያያዘም በማዕከላዊ ጎንደር ዞን 88 ተጠርጣሪ ወንጀለኞች በሕግ ቁጥጥር ስር ውለው ጉዳያቸው በመጣራት ላይ እንደሚገኝ የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ ወርቁ ኃይለማርያም ገልጸዋል።

የዞኑ ሕዝብ በሕግ ማስከበሩ ላይ ተመሳሳይ የሃሳብ አንድነት መያዙን በተለያዩ ሕዝባዊ መድረኮች በመግለጽ ላይ ነው ብለዋል።