በዲጂታል የክትትልና ሪፖርት አቀራረብ ሥርዓት ሥልጠና እየተሰጠ ነው

ግንቦት 10/2013 (ዋልታ) – የኢፌዴሪ ፕላንና ልማት ኮሚሽን ከቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ኢንስትቲዩት ጋር በመተባበር ያዘጋጁት በዲጂታል የክትትልና ሪፖርት አቀራርብ ሥርዓት (D~MRS) ላይ ለሁለተኛ ዙር የተዘጋጀ በተግባር የታገዘ ሥልጠና ከትናንት ሰኞ ግንቦት 09፣ 2013 ጀምሮ ለተከታታይ ሦስት ቀናት እየተሰጠ ይገኛል።
በዚህ የሁለተኛ ዙር ሥልጠና ላይ ንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር፣ ማዕድና ነዳጅ ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንከ፣ ግብርና ሚኒስቴር፣ አካባቢ ደንና ንብረት ለውጥ ኮሚሽን፣ ገቢዎች ሚኒስቴር፣ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ኢንስትቲዩት፣ ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር እና ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ተሳታፊ ሆነዋል፡፡
የኢፌዴሪ ፕላን እና ልማት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ እንዳልካቸው ስሜ የአስር ዓመቱ ልማት ዕቅድ ዝግጅት እና የክትትልና ግምገማ ሥርዓት በጥንቃቄ የተዘጋጀ መሆኑን የገለጹ ሲሆን፤ የግምገማ ሥርዓቶችን ለማዳበር ሪፖርት የማድረግ ሒደቱ ስታንዳርዱን ጠብቆ መሰራት እንደሚኖርበት አመልክተዋል፡፡
የክትትልና ግምገማ ሥርዓቱ ከሂደት ይልቅ ውጤትን ትኩረት ያደረገ መሆኑን ያስታወሱት አቶ እንዳልካቸው፣ የሥልጠናው ዋና አላማ አዲስ የክትትልና ግምገማ ስርዓትን በማስተዋወቅ የተዘጋጀውን አሰራር ማዳበር እንዲሁም እንደ ሀገር በቡድን የመስራት ልምዶችን ማጠናከር መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ይህ አሰራር አዲስ እና በሙከራ ደረጃ ተግባራዊ የሚደረግ ሆኖ የክትትልና ግምገማ ስርዓቱን በቴክኖሎጂ በማገዝ በአስር ዓመቱ የልማት ዕቅድ የተቀመጡ ግቦችን በግልፅ፣ በተቀናጀ ሃላፊነትና ተጠያቂነት በተሞላበት አግባብ ተፈፃሚ እንዲሆኑ የሚያግዝ መሆኑንም አብራርተዋል፡፡
በመቀጠል የፕላንና ልማት ኮሚሽን የክትትል እና ግምገማ ቢሮ ዋና ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ሰለሞን ተስፋስላሴ በክትትልና ግምገማ ፅንሰ ሃሳብ፣ አስፈላጊነቱና ጠቀሜታው እንዲሁም ስለ አስር ዓመቱ የልማት ዕቅድ የክትትልና ግምገማ ስርዓት እንዲሁም ይህን ተከትሎ በፕላንና ልማት ኮሚሽን በኩል የተዘጋጁ መመሪያዎችና አሰራሮች ዙሪያ ማብራሪያ ሠጥተዋል፡፡ በተጨማሪም የዲጂታል ክትትልና ሪፖርት አቀራረብ ሥርዓት (D~MRS) አስፈላጊነትና አላማ ላይ ገለፃ አድርገዋል፡፡
ከዚህ በማስተከተል ከቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ኢንስትቲዩት የተወከሉት አቶ ዘሪሁን ከበደ ስለ አሰራሩ አላማ፣ ዋና ዋና ገፅታዎችና አሰራሩ ምን ያህል አሁን ያለውን አሰራር እንደሚያቃልል ገለፃ ካደረጉ በኋላ ወደ ተግባር ሥልጠና በመግባት፣ ሠልጣኞች ጊዜ ወስደው በተግባር እንዲለማመዱ፣ እንዲሞክሩ እና በተግባር እንዲያዩት ተደርጓል፡፡
ቀጥሎም ከተቋማቱ የተወከሉ ተሳታፊዎች የልማት ዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርትና ዋና ዋና ቁልፍ የአፈፃፀም አመልካቾች እንዴት ሪፖርት እንደሚደረጉ የተግባር ሥልጠናውን በመውሰድ የ9 ወር ዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርቶቻቸውንም በዚሁ ሥርዓት እንዲልኩ አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡
ይኸው ሥልጠና በሁለተኛው ዙር መድረክ የተገኙ ግብዓቶችን በማካተት በቀጣይ ለሌሎች ተቋማት የሚሰጥ መሆኑም ተጠቁሟል፡፡
(በደረሰ አማረ)