ጠ/ሚ ዐቢይ አህመድ የ2013 የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብርን በይፋ አስጀመሩ

ግንቦት 10/2013 (ዋልታ) – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የ2013 የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብርን በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት በይፋ አስጀመሩ።
“ኢትዮጵያን እናልብሳት” የሚል መርህ ያለው የዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር 7 ነጥብ 7 ቢሊዮን ችግኞች ለመትከል መዘጋጀታቸው ተገልጿል፡፡
በዚህም እንደሀገር 7 ቢሊዮን ችግኞች የሚተከሉ ሲሆን ከዚህ ውስጥ በኦሮሚያ ክልል 4 ነጥብ 5 ቢሊየን ችግኞች ለመትከል መታቀዱ ተገልጿል፡፡
ለጎረቤት አገራት 1 ቢሊዮን ችግኞች የሚቀርብ መሆኑም ተጠቁሟል።
መርሃ ግብሩን በማስመልከት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ከክልል ርእሳነ መስተዳድሮችና ሚኒስተሮች እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻ አካላት ውይይት አድርገዋል።
ከዘሬ ጀምሮም ዝናብ በሚያገኙ የሀገሪቱ ክፍሎች ችግኞች የሚተከሉ ሲሆን ዝናብ የማያገኙ አካባቢዎች ደግሞ ቅድመ ዝግጅት እንደሚደርጉ ነው የተገለጸው፡፡
ለመርሃ ግብሩ ስኬት ህዝቡ የተጠናከረ ተሳትፎ እንዲያደርግ ጥሪ ቀርቧል።
(በአስታርቃቸው ወልዴ)