በጀርመን የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ለህዳሴ ግድብ 3 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አደረጉ

ግንቦት 09/2013 (ዋልታ) – “የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆችች ” በሚል መርህ ቃል በጀርመን በርሊን የኢፌዴሪ ኤምባሲ እና ፍራንክፈርት ቆንስላ ጀኔራል በጋራ አስተባባሪነት በጀርመን የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ 3 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አድርገዋል፡፡
የኢፌዲሪ የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ በጀርመን ለሚኖሩ የዳያስፖራ ወገኖች በዌብነር ማብራሪያ ሰጥተዋል።
የግድቡ ግንባታ ስራ በከፍተኛ የሀገራዊ ፍቅር ስሜት እየተከናወነ ነው መሆኑን ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያ ማንኛውም አይነት የግርጌ ተፋሰስ አገራትን ሳትጎዳ የተፈጥሮ ኃብቶቿን ማልማቷን እንደምትቀጥልም ሚኒስትሩ ተናግረዋል።
ሚኒስትሩ “ይህን የአገር ኩራት በዘመናችን ታሪክ እንድንሰራበት አሻራችንን እንድናሳርፍበት ከዚህ ትውልድ መሆናችን ከእደለኝነትም በላይ ነው” ብለዋል፡፡
ግድቡን በመላው ዓለም የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ወገኖች በቻሉት ሁሉ በመደገፍ ፍጻሜውን እውን ማድረግ እንደሚገባ ሚኒስትሩ ጥሪ አስተላልፈዋል።
በጀርመን የኢፌዲሪ አምባሳደር ሙሉ ሰለሞን ለሀገራዊ ጥሪ አፋጣኝ ምላሽ በመስጠት በተግባር የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆች በመሆን ለተገኙ የዳያስፖራ አባላት ምስጋና አቅርበው፣ የህዳሴ ግድቡ መጠናቀቅ ከፍተኛ የኢኮኖሚ መነቃቃትና ዘርፈ ብዙ ማህበራዊ በረከቶች የሚኖሩት በመሆኑ የገንዘብ ድጋፍ በማድረግ ለዚህ ታላቅ ፕሮጀክት የበኩላቸውን እንዲያበረክቱ ጥሪ አቅርበዋል።
የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ሰላማዊት ዳዊት፣ በጀርመን የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን እያደረጉ ያለውን የነቀ የልማት ተሳትፎ እና የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ድጋፍ ምስጋና አቅርበው ድጋፉ ተጠናክሮ እንዲቀጥልም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በፍራንክፈርት የሚገኘው የኢፌዴሪ ቆንስላ ጄኔራል ጽ/ቤት ቆንስል ጄኔራል አቶ ፈቃዱ በየነን በመወከል መልእክት ያስተላለፉት ወ/ሮ ኡብሀ መሐመድ የዘመናት ታሪክ ተቀይሮ ዐባይ ረግቶ ወገኖቹን ሊክስ የተቃረበ መሆኑን በመጥቀስ በተባበረ ክንድ የገንዘብ ድጋፍ በማድረግ ለዚህ ታላቅ የተቀደሰ ሥራ ሁሉም ያለ ልዩነት የበኩሉን እንዲያበረክት ጥሪ ማቅረባቸውን ከጀርመን የኢትዮጵያ ኤምባሲ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።