በጅቡቲ በደረሰ የጀልባ መስጠም አደጋ የ38 ኢትዮጵያዊያን ፍልሰተኞች ሕይወት አለፈ

ሚያዚያ 1/2016 (አዲስ ዋልታ) በጅቡቲ የባህር ዳርቻ ፍልሰተኞችን አሳፍራ ወደ የመን በመጓዝ ላይ በነበረች ጀልባ ላይ በደረሰ የመስጠም አደጋ 38 ኢትዮጵያውያን ፍልሰተኞች ሕይወት አልፏል።

በጅቡቲ ሰሜን ምስራቅ ጎዶሪያ በሚባል የባህር ዳርቻ አቅራቢያ 60 ኢትዮጵያውያን ፍልሰተኞችን አሳፍራ ወደ የመን ትጓዝ የነበረች ጀልባ ላይ በደረሰው የመገልበጥ አደጋ 38 ፍልሰተኞች ሕይወታቸውን ማጣታቸውን በጅቡቱ የኢትዮጵያ ኤምባሲ መረጃ አመላክቷል።

በጅቡቲ የኢፌዲሪ ሚሲዮንም አደጋው ከደረሰ በኋላ ወደ ስፍራው በመጓዝ የአደጋውን መንስኤ በማጣራት ላይ እንደሚገኝ ገልጿል።

ሚሲዮኑ በዚህ አሳዛኝ ክስተት የተሰማውን ጥልቅ ሀዘን ገልፆ፤ ከጅቡቲ ወደ መካከለኛው ምስራቅ አገራት የሚደረገው ህገ ወጥ ጉዞ እጅግ አደገኛ ከመሆኑም በላይ በየጊዜው የዜጎችን ሕይወት እያሳጣ እንደሚገኝ አስገንዝቧል።

ሚሲዮኑ ዜጎች በህገ ወጥ ደላሎች የሀሰት ስብከት በመታለል ውድ ሕይወታቸውን አደጋ ላይ ጥለው በዚህ አደገኛ የጉዞ መስመር ከመንቀሳቀስ እንዲቆጠቡ አሳስቧል።