አሶሳ-ከተሞቻችን

“የወርቅ ምድር” በሚል የምትሞካሸው አሶሳ ከተማ በ1929 ዓ.ም በንጉስ ሼህ ሆጀሌ አልሀሰን የተቆረቆረች ሲሆን የቤንሻጉል ጉምዝ ክልላዊ መንግስት ዋና መቀመጫ ናት።

ከመዲናችን አዲስ አበባ በስተሰሜን ምዕራብ አቅጣጫ 687 ኪ.ሜ ርቀት ላይ የምትገነው አሶሳ ከባህር ጠለል በ1570 ሜትር ከፍታ ላይ ስትገኝ ሜዳማ የመሬት አቀማመጥ እና ቀይ የሸክላ አፈር ተፈጥሯዊ ገፅታ አላት።

አሁን ያለውን ስያሜ ከማግኘቷ በፊት “አጾጾ” ተብላ ትጠራ የነበረ ሲሆን “አሶሳ” ብለው የሰየሟት ሼህ ሆጀሌ እንደሆኑ እና ትርጓሜውም “መሰባሰብ” የሚል እንደሆነ ታሪኳ ያስረዳል።

ቆላማ የአየር ንብረት ያላት አሶሳ የቀርከሃ ተክልን ጨምሮ ማንጎ፣ ጥጥ፣ ብርቱካን፣ ሸንኮራ አገዳ እና የጎማ ዛፍ አብቃይ ምድር ስትሆን በእምነበረድ እና ወርቅ ምርቶቿም ትታወቃለች።

በከተማዋ ውስጥ በቱሪስት መዳረሻነት የሚታወቀው እና በሺህ ሆጀሌ ስም የሚጠራ የችሎት አዳራሽ የሚገኝ ሲሆን በተጨማሪም የልጃቸው አሻፊ ሆጀሌ መቃብር ቦታ እና ታሪካዊው ያዓ-መሰራ መስጊድ ይገኛል።

አሶሳ በውስጧ የተለያዩ ሰፈሮችን የያዘች ሲሆን ድርቤ ሰፈር፣ ኮሚሽን ሰፈር፣ ጤና ሰፈርና ሰላም ሰፈር ጥቂቶቹ ናቸው። ከተማዋ የራሷ አየር ማረፊያ እና ስታድየም አላት።

የኢንዚ ተራራ በአሶሳ የሚገኝ ልዩ የሆነ የከተማዋ መገለጫ ሲሆን ነፋሻማ አየር ያለው እና የከተማዋን አጠቃላይ ገፅታ ለመቃኘት የሚያስችል ተፈጥሮ ነው።

አሶሳ ዩኒቨርሲቲን ጨምሮ፣ ፋሮ አንደኛ ደረጃ፣ አሶሳ ሰላም በር፣ አሶሳ አንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ እንዲሁም የግብርና እና ጤና ኮሌጆች በከተማው የሚገኙ የትምህርት ተቋማት ናቸው።

ከእግር ኳሱ ዓለም ታዋቂው የብሔራዊ ቡድን ተጫዋች ሳላዲን ሰይድ እና የቀድሞ ፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት የሆኑት መአዛ አሸናፊ ከአሶሳ ምድር ከተገኙ የሀገር ባለውለታዎች ውስጥ ተጠቃሽ ናቸው።

በወርቅ ምድሯ አሶሳ ከተማ ተወልዳችሁ ያደጋችሁም ሆነ በተለያየ አጋጣሚ አይታችኋት ልዩ ትዝታን ያተረፋችሁ ትዝታችሁን አጋሩን።

መልካም ሳምንት!!!!!!

በአዲስዓለም ግደይ