በጋምቤላ ክልል መጪው ሀገራዊና ክልላዊ ምርጫ ስኬታማ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የፀጥታ አካላት በትኩረት ሊሰሩ ይገባል – አቶ ኡሞድ ኡጁሉ

ሚያዝያ 18/2013(ዋልታ) – በጋምቤላ ክልል መጪው ሀገራዊና ክልላዊ ምርጫ ሰላማዊና ፍትሃዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የፀጥታ አካላት ጠንክረው ሊሰሩ እንደሚገባ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ አሳሰቡ፡፡

ስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ለማስቻል እንዲሁም በክልሉ ወቅታዊ የፀጥታ ሁኔታ ዙሪያ ውይይት ተካሂዷል፡፡

ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ በክልሉ ባለፉት ሶስት ዓመታት የታየውን ሰላም ይበልጥ በማጠናከር ሀገራዊና ክልላዊ ምርጫው ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መልኩ እንዲጠናቀቅ የፀጥታ አካላት ከወገንተኝነት በፀዳ መልኩ ሊሰሩ ይገባል፡፡

የፀጥታ ሀይሉን ማጠናከር እንደሚያስፈልግ ጠቅሰው በክልሉ በአንዳንድ ቦታዎች አልፎ አልፎ የሚስተዋሉ የፀጥታ ችግሮችን ለመቅረፍ ሁሉም አካላት በቅንጅት መሰራት እንደሚገባ ጠቅሰው ምርጫውን በስኬት ለማጠናቀቅ ጉዳዩ ለመንግስትና ለምርጫ ቦርድ ብቻ የሚተው ሳይሆን ከህብረተሰቡ ጀምሮ የሁሉም አካላት ትብብር እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።

በክልሉ የሚፎካከሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምርጫው ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ አባላቶቻቸውን አስተባብረው በመስራት የበኩላቸውን ሚና መወጣት ይኖርባቸዋል።

የፖሊስ አካላትም ከየትኛውም የፖለቲካ ወገንተኝነት በፀዳ መልኩ ሁሉንም እኩል ማገልገል አንደሚገባ ከኢፕድ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።