በሀሰተኛ ሰነድ ተጠቅሞ ወደ ሀገር ውስጥ ሊገባ የነበረ ገጀራ ተያዘ

ሚያዝያ 18/2013(ዋልታ) – ከፌደራል ፖሊስ ወንጀል መከላከል ጋር በጋራ በተደረገው ማጣራት ሀሰተኛ ሰነድን ተጠቅሞና ከፌደራል ፖሊስ ፍቃድ ያልተሰጠው በአስመጪ ዳዊት የማነ ስም ብዛቱ 186 ሺህ 240 የሆነ የእጅ ገጀራ በአራት ባለ 20 ጫማ  ኮንቴይነሮች ከቻይና ተጭኖ ተጓጉዞ  ሞጆ ጉምሩክ ከደረሰ በኃላ መያዙን የገቢዎች ሚኒሰቴር  አሰታወቀ።

እቃው በዲክላራሲዮን ቁጥር 4-1919/21 ተመዝግቦ ወደ ሀገር ዉስጥ እንዲገባ ከፌዴራል ፖሊስ የተፈቀደለት በማስመሰል ሐሰተኛ ሰነድ አዘጋጅቶ ለገቢ ዕቃ አወጣጥ የሰነድ መርማሪው አቅርቦ ሰነዱ ተመርምሮ ከ7 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር በላይ ቀረጥና ታክስ ተከፍሎበት እቃው ወደ አገር ውስጥ እንደገባም ሚኒስቴሩ አስታውቋል።

ከተለቀቀ በኃላ በጉምሩክ ኮሚሽን እና በሞጆ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኢንተለጀንስ በኩል ክትትል ተደርጎ የቀረበው ሰነድ ሲጣራ ሐሰተኛና ወደ ሀገር ዉስጥ እንዲገባ ከፌዴራል ፖሊስ ፈቃድ ያልተሰጠው በመሆኑ መያዙን የገቢዎች ሚኒሰቴር አስታውቋል።

ጉዳዩ ከ15 ቀን በፊት የተፈጸመ ቢሆንም፤ አስመጪው ያቀረብኩት ሰነድ ህጋዊ ነው በማለት ቅሬታ ስላቀረበ ከፌደራል ፖሊስ ወንጀል መከላከል ጋር በጋራ ሲጣራ ቆይቶ በተደረገው ማጣራት ሰነዱ ሐሰተኛ እና ከፌደራል ፖሊስ ፍቃድ ያልተሰጠው መሆኑ ተረጋግጧል ነው ያለው ሚኒስቴሩ።

ፌዴራል ፖሊስ ለሞጆ የወንጀል ምርመራ ማስተባባሪያ ፅ/ቤት መረጃዉን በመስጠት በተደረገው እልህ አስጨራሽ ክትትል የእቃው ባለቤትና ትራንዚተሩ ተይዘው ጉዳዩ በምርመራ ላይ ይገኛል::

ገጀራ ክልከላ ከተደረገባቸው እቃዎች አንዱ ሲሆን ከፌደራል ፖሊስ ሕጋዊ ፈቃድ ሳያገኙ ማስገባት እንደማይቻል ተገልጿል።

በማህበራዊ ሚዲያ ገጾች በጉምሩክ ኮምሽን ባለሙያ እቃው እንዲወጣ የተፈቀደበት ደብዳቤ በማስመሰልና ሐሰተኛ የደብዳቤ ፎቶ በመጠቀም አስመጪው ሕጋዊ እንደሆነ ተደርጎ የሚሰራጨው መረጃ ሐሰተኛ መሆኑን ሚኒስቴሩ አሰታውቋል።