በጋሞ ዞን የምርጫ ቁሳቁስ ወደ የምርጫ ጣቢያዎች እየተሰራጨ ነው

ሰኔ 12/2013 (ዋልታ) – በደቡብ ክልል ጋሞ ዞን የምርጫ ቁሳቁስ ወደ የምርጫ ጣቢያዎች እየተሰራጩ መሆናቸው ተገለጸ።

በዞኑ አስር የምርጫ ክልሎች እና 810 የምርጫ ጣቢያዎች የሚገኙ ሲሆን፣ አስር የፖለቲካ ፓርቲዎች ይውዳዳራሉ ተብሏል።

በምርጫ ጣቢዎች በሚገኙ 2 ሺህ 24 የምርጫ አስፈጻሚዎች አማካኝነት 599 ሺህ 964 መራጮች የምርጫ ካርድ መውሰዳቸውም ተገልጿል።

የምርጫ ቁሳቁስም ከዞኑ ዋና ከተማ አርባ ምንጭ ወደየምርጫ ጣቢያዎች አየተጫኑ መሆኑን የዞኑ የምርጫ አስተባባሪ አቶ አብርሃም አንጀሎ ተናግረዋል።

የምርጫ ቁሳቁስ መዘግየት በታየባቸው ጨንቻና ዲታ አካባቢም ቢሆን ዛሬ ሰዓት ይደርሳል ብለው እንደሚጠብቁና የየአካባቢው የመንግስት አስተዳደር የማጓጓዣ ተሽከርካሪዎች ዝግጁ አድርገው እየጠበቁ መሆናቸውን አቶ አብርሃም ገልፀዋል።

ምርጫውን ውጤታማ ለማድረግ ከፀጥታ ተቋማት ጋር በቅንጅት አየተሰራ መሆኑንም አመልክተዋል።

የጋሞ ዞን ፖሊስ መምሪያ ኃላፊ ምክትል ኮማንደር ደግፌ ደበላ በበኩላቸው፣ ምርጫውን ውጤታማ ለማድረግ ፖሊስ፣ ሚሊሻና አቃቤ ህግ በጋራ የሰላምና ፀጥታ ሥራውን በመሥራት 18 አደረጃጀቶች በማዋቀር ስምሪት ተሰጥቷል ብለዋል።

የፖሊስ አባሉ ምርጫውን በገለልተኝነት እንዲያካሂድ ስልጠናና መመሪያ ተሰጥቶት የሥራ ስምሪት መደረጉንም የዞኑ  ፖሊስ  ኃላፊ ገልዋፀል።

የምርጫው እለት የኮቪድ-19 ጥንቃቄ እንዲኖር የጋሞ ዞን ምርጫ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ከተወዳዳሪ ፖርቲዎች፣ ከመንግስትና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ምክክር ማድረጉንና ሳኒታይዘር የማዘጋጀት እንዲሁም እርቀትን በጠበቀ መልኩ ምርጫውን ለማካሄድ እንደተዘጋጀም ተገልጿል።

(በምንይሉ ደስይበለው)