ሁሉም ዜጋ ለሀገር ሰላም እና መረጋጋት በኃላፊነት መስራት እንዳለበት ተገለጸ

በሻሸመኔ በተካሄደው የእርቅ እና የሰላም ኮንፍረንስ ላይ የነበሩ ተሳታፊዎች የሚዲያ ተቋማትን ጨምሮ ሁሉም ዜጋ ለሀገር ሰላም እና መረጋጋት መስራት እንዳለበት አሳሰቡ።

የጉባኤው ተሳታፊ የነበሩ አባ ገዳዎች፣ የሀይማኖት መሪዎች፣ ሀደ ሲንቄዎች እና የሻሸመኔ ከተማዋ ነዋሪዎች ካለፉት ስህተቶች በመማር እና ይቅር በመባባል የበለፀገች ሀገር መገንባት አለብን ብለዋል።

መዝረፍ እና ሰዎችን መጉዳት የገዳ ስርዓት አይደለም ያሉት የጉባኤው ተሳተፊ አባገዳዎች በቄሮ ስም በከተማዋ እና አከባቢዋ ላይ ጉዳት ያደረሱ ሰዎች ከማንም ዘር እና ኃይማኖት አለመሆናቸውን አስረግጠዋል።

ከዚህ በኋላ በአካባቢያቸው ተመሳሳይ ችግር እንዳይፈጠር ኃላፊነት እንወስዳለን ያሉት አባገዳዎቹ፣ ከዚህ በፊትም ሆነ ከዚህ በኋላ በኃይማኖትና በዘር ሽፋን ጉዳት ያደረሱም ሆኑ የሚያደርሱትን በመከታተል ለህግ እንዲቀርቡ እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

በከተማዋ የኃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች እና ወጣቶች የጉዳቱ ሰለባ የሆኑ ወገኖችን በፍጥነት ወደ መደበኛ ህይወታቸው እንዲመለሱ መስራት እንዳለባቸው አሳስበዋል።

ከተማዋ ወደ ቀድሞ ሰላሟ በመመለሷ ደስተኛ መሆናቸውን በመድረኩ የተሳተፉ የከተማዋ ነዋሪዎች የዜጎች እና የሀገር ሰላም በዘላቂነት እንዲጠበቅ መንግስት የህግ የበላይነትን እንዲያረጋግጥ ጠይቀዋል።

ከዚህም በተጨማሪ በመድረኩ ላይ ቃል የተገቡ የአብሮነት፣ አንድነት እንዲሁም ለሰላም ዘብ መቆም ተግባራዊ መሆን አለበትም ብለዋል።

በመድረኩም ላይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ም/ስራ አስኪያጅ ቀሲስ በላይ ታደለ  እና የኢትዮጵያ ኃይማኖት ጉባኤ ም/ቦርድ ሰብሳቢ ሼህ መሀድ ሲራጅ ያለፈውን ይቅር በመባባል ስለሰላም እና አንድነት መሥራት እንዳለበት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

የሻሸመኔ ከተማ ከንቲባ ጉታ ላቾሬ መንግስት የዜጎችን ሰላም አስተማማኝ ለማድረግ በቁርጠኝነት አየሰራ መሆኑን ገልፀው፣ ሻሸመኔ ልማቷ እንዲፋጠን የኢንቨስትመንት ከተማ በማድረግ ብልፅግናን እናረጋግጣለን ብለዋል።

(በሚልኪያስ አዱኛ)