በጎንደር በተከሰተው ግጭት ከ370 በላይ ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር ዋሉ

ሚያዝያ 21/2014 (ዋልታ) በጎንደር ከተማ አስተዳደር ከተከሰተው ግጭት ጋር በተያያዘ 373 ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን የአማራ ክልል ሰላምና ደኅንነት ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮ ኃላፊ ደሳለኝ ጣሰው ከጎንደር የፀጥታ ሁኔታ ጋር በተያያዘ በሰጡት መግለጫ በከተማዋ ላይ በተፈፀመው ችግር ምክንያት ችግሮቹን እንዲሰፉ የሚያደርጉ አካላት መኖራቸውን ገልፀው ጥፋተኞቹን የመያዝ ተግባር እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል።

ከሀገር ሽማግሌዎች፣ ከሃይማኖት አባቶች እና ከሌሎች የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር በመወያየት ወደ ሰላም ከተመለሰ በኋላ ትናንት እንደገና እኩይ ዓላማቸውን ለማስፈጸም ፍላጎት በነበራቸው አካላት በተነሳ ግጭት የሰው ሕይወት ማለፉንና ንብረት መውደሙን አስታውቀዋል።

ትናንት ዳግም ግጭት ለመቀስቀስ የሞከሩ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን የገለጹት ኃላፊው በተወሰደው እርምጃ ጎንደር ወደ ሰላም እየተመለሰች እንደሆነና አስተማማኝ የሚሆነው በጥፋት የተሳተፉትን በሙሉ ስንይዝ ነው ብለዋል።

ይህ ዜና እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ የፀጥታ ኃይሉ በሠራው ሥራ 373 ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን አሚኮ ዘግቧል።

ኃላፊነታቸውን ያልተወጡ የፀጥታ ኃይሎችንና መሪዎችን በሕግ ተጠያቂ እያደረገ መሆኑንም ገልፀዋል።

የፀጥታ ኃይሉ በተቀናጀ መንገድ እርምጃ እንዲወስድ አቅጣጫ መቀመጡን ያስታወቁት ኃላፊው ኃላፊነቱን ያልተወጣ ሁሉ ይጠየቃል ነው ያሉት።

ተጠርጣሪዎች ተለቅመው እስኪያዙ ድረስ ከፀጥታ ኃይሉ ውጭ ያለው መሣሪያ እንዳይወጣ አቅጣጫ መቀመጡንና የፀጥታ ኃይሎችን ልብስ ከአባል ውጭ ለብሶ በሚገኝ አካል ላይ እርምጃ እንደሚወሰድ ገልፀዋል።

ከከተማ የሚወጣም ሆነ የሚገባ መሣሪያ እንዳይኖር ታግዷል ያሉት ኃላፊው ከሕዝብ ጋር የሚቆሙትና ለሕዝብ መስዋእትነት የሚከፍሉ የራሳቸው ትጥቅ ያላቸው ጀግኖች ፋኖዎች ከመንግሥት ሥምሪት እስከሚሰጣቸው ድረስ በቤታቸው ሆነው እንዲጠብቁም ጥሪ አቅርበዋል።

በፋኖ ስም በሚነግድ አካል ግን አስፈላጊው እርምጃ ይወሰዳል ነው ያሉት።

ለአንድ ወገን በማድላት ችግር እንዲባባስ የሚያደርጉ አካላት ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡም አሳስበዋል።