ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ በኬኒያ የቀድሞ ፕሬዝዳንት አስከሬን ሽኝት መርኃ ግብር ላይ ተገኙ

ሚያዝያ 21/2014 (ዋልታ) ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ የኬንያ 3ኛ ፕሬዝዳንት በነበሩት ምዋይ ኪባኪ አስከሬን ሽኝት መርኃ ግብር ላይ ተገኙ፡፡

በናይሮቢ ኒያዮ ብሔራዊ ስታድዮም በተካሄደው መርኃ ግብር ለመሳተፍ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴን ጨምሮ የደቡብ አፍሪካው ሲሪል ራማፎሳ እና የደቡብ ሱዳኑ ሳልቫ ኪር ማያርዲት እንዲሁም ሌሎች የተለያዩ አገራት መሪዎችና የቀድሞ ፕሬዝዳንቶች ተገኝተዋል።

ፕሬዝዳንቷ በመርኃ ግብሩ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት የቀድሞው ፕሬዝዳንት ምዋይ ኪባኪ በስልጣን ዘመናቸው ቀጣናዊ ትስስር ላይ በርካታ ሥራዎችን ስለመስራታቸው እና በእርሳቸው ዘመን በኢትዮጵያ እና ኬንያ መካከል ትብብርን የሚያጠናክሩ በርካታ ስምምነቶች ስለመፈረማቸው ገልፀዋል።

ምዋይ ኪባኪ የመጀመሪያውን ተፎካካሪ ፓርቲ በመምራት ሁለት ጊዜ በምርጫ ተመርጠው እ.ኤ.አ ከ2002 እስከ 2013 በፕሬዝዳንትነት አገልግለዋል።

ከፍተኛ ትምህርታቸውን በምጣኔ ሃብት ዘርፍ በዩጋንዳና በእንግሊዝ ተከታትለው በመጀመሪያ በአስተማሪነት ቀጥለውም በሀገራቸው ፋይናንስ ሚኒስትርነት ለ13 ዓመታት እንዲሁም በምክትል ፕሬዝዳንትነት ለ10 ዓመታት አገልግለዋል።

በመሪነት ጊዜያቸውም ኬንያ ዘላቂ የሆነ ምጣኔ ሃብት እንድታዳብር በማድረጋቸው እና ሙስናን መታገል ላይ ባላቸው ጠንካራ አቋም በሕዝባቸው ይመሰገናሉ።

በተጨማሪም 1 ሚሊዮን ታዳጊ ህፃናት ትምህርት እንዲማሩ መዋቅሩን በማስተካከል ትልቅ አሻራ ትተው ያለፉ ስለመሆናቸውም ይነገራል።

የኬንያ ሪፐብሊክ 3ኛው ፕሬዝዳንት የነበሩት ምዋይ ኪባኪ በ90 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት ከሳምንት በፊት መሆኑን ኢብኮ በዘገባው አስታውሷል።