በጦርነቱ ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች እየተደረገ ያለው የስነ-ልቦና እና ማህበራዊ ድጋፍ ተጠናክሮ ይቀጥላል

የካቲት 7/2014(ዋልታ) በጦርነቱ ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች እየተደረገ ያለው የስነ-ልቦና እና ማህበራዊ ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የጤና ሚኒስቴር ገለጸ።

በጦርነቱ ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች የስነ-ልቦናና ማህበራዊ ድጋፍ መስጠት የሚያስችል የአሰልጣኞች ስልጠና በአፍሪካ የአመራር ልህቀት አካዳሚ መሰጠት ተጀምሯል፡፡

የሕወሃት ሽብር ቡድን በአፋርና አማራ ክልሎች በወረራ በቆየባቸው አካባቢዎች የጤና ተቋማት፣ትምህርት ቤቶችና ሌሎች የሕዝብ መገልገያ ተቋማትን ማውደሙና መዝረፉ ይታወቃል።

በንጹሃን እና አቅመ ደካማ ዜጎች ላይ ጥቃት በመፈጸም በርካታ ዜጎችን ከመኖሪያ ቀያቸው እንዲፈናቀሉ ማድረጉም ይታወሳል።

ይህም በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ላይ ካሳደረው አሉታዊ ተጽእኖ ባሻገር በማኅበረሰቡ ላይ ከፍተኛ የሆነ ማኅበራዊና ሥነ-ልቦናዊ ቀውስ አስከትሏል፡፡

ከዚህ አኳያ የጤና ሚኒስቴር በጦርነቱ ጉዳት የደረሰባቸው ዜጎች የስነ-ልቦና ድጋፍ እንዲያገኙ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑን አስታውቋል፡፡

በዛሬው እለትም የዚሁ ስራ አካል የሆነና በጦርነቱ ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች የሥነ-ልቦና፣ ማኅበራዊና የአእምሮ ጤና ድጋፍ መስጠት የሚያስችል የአሰልጣኞች ሥልጠና ተጀምሯል።

የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ በዚህ ወቅት ስልጠናው በዋናነት ከችግሩ ስፋት አንጻር ሁሉንም ተጎጂዎች ተደራሽ ማድረግን ያለመ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ስልጠናው በዋናነት የጤና ባለሙያዎችን፣ ጾታዊና ህጻናት ጥቃትን ለመከላከል የሚሰሩ አካላትን እንዲሁም የማህበረሰብ መሪዎችን ታሳቢ ባደረገ መልኩ መዘጋጀቱን አብራርተዋል፡፡

ሚኒስቴሩ ከዚህ ቀደም በጦርነቱ ጉዳት የደረሰባቸው ዜጎች የስነ-ልቦና እና ማህበራዊ ድጋፍ እንዲያገኙ ሲሰራ መቆየቱንም ነው ያብራሩት፡፡

በዚህም ባለፉት አራት ወራት ብቻ ከ42 ሺህ 842 በላይ ለሚሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች የሥነ-ልቦናና የአእምሮ ጤና ሕክምና ድጋፍ እንደተደረገላቸው ጠቁመዋል።

የአንድ ማዕከል አገልግሎት በማቋቋም ጾታዊ ጥቃት ለደረሰባቸው ወገኖች የሕክምና ድጋፍ ለመስጠት እየተሰራ መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል፡፡

የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ዴኤታ ወይዘሮ አየለች እሸቴ በበኩላቸው በጦርነቱ ጉዳት የደረሰባቸው የማኅበረሰብ ክፍሎች አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያገኙ ሁሉም የበኩሉን ድርሻ ሊወጣ እንደሚገባ አንስተዋል፡፡

በጦርነቱ ብቻ ሳይሆን በድርቅ ለተጎዱ የማኅበረሰብ ክፍሎችም የሥነ-ልቦና ድጋፍ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።

የተባበሩት መንግሥታት የሕጻናት አድን ድርጅት (ዩኒሴፍ) በኢትዮጵያ ተጠሪ ዳይሬክተር ጂያን ፍራንኮ፤ ጉዳት ለደረሰባቸው የማኅበረሰብ ክፍሎች የሥነ-ልቦና ድጋፍ ለማድረግ እየተሰራ ነው ብለዋል።