በ25 ሚሊየን ብር ወጪ የተገነባው የይስማ ንጉሥ ሙዝየም ነገ ይመረቃል

ለዓድዋ ጦርነት ምክንያት የሆነውና የውጫሌ ውል በተፈረመበት ታሪካዊ ቦታ ላይ የተሰራው የይስማ ንጉስ የሙዝየም ግንባታ ተጠናቆ  ነገ የፌዴራልና የክልል የመንግስት ስራ ኃላፊዎች የአካባቢው ማህበረሰብ በተገኙበት ይመረቃል፡፡

የዉጫሌ ዉል በ1881ዓ.ም አጼ ሚኒልክ ከጣሊያን ጋር የተፈራረሙበት ታሪካዊ ቦታ ላይ በ25 ሚሊየን ብር በሆነ ወጪ  ሙዚየም፣ ካፌና የመግቢያ በር የኢትዮጵያ ቁጥር ፲፯ (17) አምሳል ተገንብቶ ተጠናቋል፡፡

የባህል ማዕከሉ የኢትዮጵያን ታሪክ የሚያሳዩ መረጃዎችን ያካተተ ሲሆን የቀለም ቅቡም  የአሸናፊነትና የተሸናፊነትን እንዲወክል ተደርጎ የተዘጋጀ መሆኑ ተገልጿል፡፡

በማዕከሉ ጣሪያ ላይ የአሸናፊነትን የሚያመለክት የእጅ ምልክት መሰራቱም ነው የተገለጸው ።

ለታሪካዊው የአድዋ ጦርነት መነሻ በመሆን ከሚጠቀሱ ምክንያቶች መካከል የውጫሌ ውል ቀዳሚው ነው፡፡

የውጫሌ ውል በአጼ ምኒሊክ እና በጣሊያን ንጉሥ ኡምቤርቶ ወኪል ኮንት አንቶሎኒ መካከል ወረኢሉ ቦሩ ሜዳ አካባቢ ውጫሌ በሚባል ቦታ ሚያዚያ 25 ቀን 1881ዓ.ም የተደረገ የውል ስምምነት ነው፡፡

ጣሊያን የውጫሌ ውል የንግድና የፍቅር ነው በማለት ብትቀርብም ከመነሻው ጀምሮ ብዙ ጥርጣሬ፣ ክርክር እና ተቃውሞ በኢትዮጵያውያን ዘንድ ሲሰማ እንደነበር ታሪክ ያስታውሳል፡፡

በተለይ በአንቀጽ 3 እና 17 ምክንያት የተነሳው ተቃውሞ በቀጥታ በሁለቱ አገራት መካከል ለተካሄደው ጦርነት መነሻ እንደሆነ ይታመናል፡፡

በአንቀጽ 17 አማካኝነት ጣሊያን አምታች የሆነ ቃል በመጠቀም የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት በመገርሰስ የጣልያን ሞግዚት እንድትሆን ቀዳዳ እያበጀች መሆኑ ሲታወቅ ለነፃነቱ ቀናኢ በሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ ዘንድ ከፍተኛ ቁጣን ቀስቅሷል፡፡

በዚህ ጊዜ እቴጌ ጣይቱ “እኔ ሴት ነኝ፣ ጦርነት አልወድም፡፡ ግን እንዲህ መሳዩን ውል ከምቀበል ጦርነት እመርጣለሁ፡፡” ይስሙ ንጉሥ!” የሚል ታሪካዊ ንግግር አድርገዋል፡፡

ይሄን ንግግራቸውን ተከትሎም የውጫሌ ውል የተፈረመበት ቦታ “ይስማ ንጉሥ” በሚል መሰየሙን ከባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ያገኘኘው መረጃ ያመላክታል።