በ5.5 ቢሊየን ብር ድጋፍ በኢንዱስትሪ ዘርፍ ላይ ለሚሰማሩ ዜጎች የሥራ እድል ለመፍጠር እየተሰራ ነው

በኢትዮጵያ ከልማት ባንክ በተገኘ 5.5 ቢሊየን ብር ድጋፍ አነስተኛ እና መካከለኛ ኢንዱስትሪ ዘርፍ ላይ ለሚሰማሩ ዜጎች የስራ እድል ለመፍጠር በዝግጅት ላይ መሆኑ ተገለጸ፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አበቤ ችግሮችን በመቅረፍ ዘላቂ የሥራ እድል ለዜጎች ለመፍጠር ሁሉም ሊረባረብ እና የሚመለከታቸው አካላት በቅንጅት ሊሠሩ እንደሚገባ ተናግረዋል።

በሀገሪቷ 20 ሺህ የሚደርሱ አምራች የአነስተኛ እና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎች የሚገኙ ሲሆን፣ እነዚህንም ሆነ አዳዲሶችን ቀጥታ ተጠቃሚ ለማድረግ ከልማት ባንክ የተገኘው ድጋፍ ፋይዳው የላቀ መሆኑን የገለፁት ወ/ሮ አዳነች፣ ኢንዱስትሪውን በማዘመን እና በአግባቡ በመጠቀም በከተማዋ  ያለውን ስራ አጥነትን መቅረፍ ይቻላል ብለዋል።

የፌዴራል አነስተኛ እና መካከለኛ ኢንዱስትሪ ዳይሬክተር አቶ አስፋው አበበ በበኩላቸው፣ በአዲስ አበባ ከተማ አነስተኛ እና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ዘርፍ በተያዘው  አመት ለበርካታ ስራ አጥ ዜጎች የሥራ እድል ለመፍጠር እየተሠራ በመሆኑ ለወጣቶች እና ሴቶች ሰፊ የስራ እድል ይፈጥራል ብለዋል።

ድጋፉ ስራ ፈጣሪ ለሆኑ ዜጎች ሁሉ ከተያዘው ወር ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚሆን የተናገሩት አቶ አስፋው፣ ከዚህ ቀደም ይደረግ የነበረው ድጋፍ ጥናት ላይ ያልተመሠረተ እና ቅንጅታዊ አሰራር ያልታየበት በመሆኑ ከዘርፉ ሊገኝ የሚገባውን ውጤት ማግኘት አልተቻለም ብለዋል።

በምክክር መድረኩ የአነስተኛ እና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎች አፈፃፀም የሚዳስስ ጥናታዊ ፅሁፍ  የፌደራል አነስተኛ እና መካከለኛ ኢንዱስትሪ ዳይሬክተር አቶ አስፋው አበበ ያቀረቡ ሲሆን፣ የግንዛቤ እጥረት፣ የፋይናንስና ማሽነሪ አቅርቦት እጥረት፣ የጥሬ እቃ እና የገበያ ትስስር አለመኖር፣ እንዲሁም የመስሪያ እና የመሸጫ ቦታ እጥረት ዘርፉ የሚፈለገውን ያህል ውጤታማ እንዳይሆን አድርጎታል ተብሏል፡፡

ከአመራሩ አንስቶ እስከ ታችኛው የማህበረሰብ አካላት በሀገር ውስጥ ለሚመረቱ ምርቶች ያለው ዝቅተኛ አመለካከት የመካከለኛ እና አነስተኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪው እንዳይጎላ አስተዋፅኦ  ከፍተኛ መሆኑም በመድረኩ ተገልጿል።

(በድልዓብ ለማ )