የኃይማኖት ተቋማት የኤችአይቪ/ኤድስ ስርጭትን ለመቀነስ ሚናቸውን እንዲያጠናክሩ ጥሪ ቀረበ

የኃይማኖት ተቋማት እና መሪዎች የኤችአይቪ/ኤድስ ስርጭትን ለመቀነስ በሚሰራው ስራ ሚናቸውን እንዲያጠናክሩ ጥሪ ቀረበ፡፡

በፀረ ኤችአይቪ/ኤድስ መድኃኒት ቁርጠኝነትና ታካሚዎች ህክምናቸውን በመውሰድ በቀጣይነት በመቆየት ላይ የሚመክር ከፍተኛ የአድቮኬሲ ስብሰባ እየተካሄደ ነዉ።

ስብሰባውን ያስጀመሩት የጤና ሚኒስትር ዶ/ር ሊያ ታደሰ ኤችአይቪ/ኤድስ ወደ ኢትዮጵያ ስገባ ስርጭቱን በመቀነስ ውስጥ የኃይማኖት ተቋማት ድርሻ ከፍተኛ እንደነበር በማስታወስ፣ አሁንም የኃይማኖት ተቋማት እና የኃይማኖት መሪዎች ሚናቸው መጠናከር አለበት ብለዋል።

“ቅዱሳት መፅሐፍት የፀረ ኤችአይቪ/ኤድስ መድኃኒትን መውሰድ ይፈቅዳሉ” በሚል መርህ ሀሳብ የኻይማኖት አባቶች ቫይረሱ በደማቸው ያለባቸውን ሰዎች የፀረ ኤችአይቪ/ኤድስ መድኃኒትን እንድወስዱ ከኃይማኖት አስተምህሮ ጋር አያይዘው እንዲያስተምሩም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በመድረኩ የኢትዮጵያ ኃይማኖት ተቋማት ጉባዔ ከአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት (USAID) ባገኘው የገንዘብ ድጋፍ ለኃይማኖት ተቋማት፣ ጤና ተቋማት እና ሌሎች ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ የኤችአይቪ/ኤድስ ስርጭትን ለመቀነስ የሚያስችል ፕሮጀክት ይፋ ሆኗል።

የፕሮጀክቱ መክፈቻ ስነስርዓት ላይ የኢትዮጵያ ኃይማኖት ተቋማት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ዑመር ኢድሪስ፣ የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ፣ የሰራተኛ እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ እና የተለያዩ የኃይማኖት መሪዎች ተገኝተዋል።

(በመስከረም ቸርነት)