በ6 ወራት ውስጥ 149 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር ገቢ ተሰበሰበ

በ2013 በጀት ዓመት የመጀመሪያው ስድስት ወራት 149 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር ገቢ መሰብሰቡን የገቢዎች ሚኒስቴር አስታወቀ።
የገቢዎች ሚኒስትር ላቀ አያሌው በመጀመሪያው ስድስት ወራት 146 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር ገቢ ለመሰብሰብ ታቅዶ 149 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር መሰብሰብ መቻሉን ገልጸው፤ ይህም የእቅዱን 101 ነጥብ 58 በመቶ ማሳካት መቻሉን አመላክተዋል።
አፈጻጸሙ ከባለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በ17 በመቶ ብልጫ እንዳለውም ጠቁመዋል።
በዚህም ከሀገር ውስጥ 93 ነጥብ 34 ቢሊዮን ብር ፣ የወጪ ንግድ ቀረጥና ታክስ 55 ነጥብ 75 ቢሊዮን ብር እንዲሁም ከሎተሪ የተጣራ ገቢ 130 ነጥብ 02 ሚሊዮን ብር ተሰብስቧል።
ሀገሪቱ በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ውስጥ ሆና እንዲሁም በህግ ማስከበር ምክንያት በትግራይ ክልል በገቢዎችና ጉሙሩክ ቅርንጫፎች ለሶስት ወራት ያህል ገቢ ያልተሰበሰበበት ሁኔታ እያለ አፈጻጸሙ ካለው ነባራዊ ሁኔታ አንጻር ሲታይ የተሻለ መሆኑንም አቶ ላቀ ገልጸዋል።
ውጤቱ ሊመዘገብ የቻለው አብዛኞቹ ግብር ከፋዮች ምክንያት ሳይደረድሩ ግብራቸውን በወቅቱ በመክፈላቸው፣ የገቢዎች ሚኒስቴር፣ የጉምሩክ ኮሚሽን እና የብሄራዊ ሎተሪ አመራሮችና ሰራተኞች በየስራ ስምሪታቸው በቁርጠኝነት በመስራትና ጠንካራ ድጋፍና ክትትል በማድረግ እንዲሁም አጋር አካላት ያለሰለሰ ድጋፍ እና ትብብር በማድረጋቸው መሆኑን ከገቢዎች ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ አመላክቷል።