ባለስልጣኑ በስድስት ወራት 313.6 ሚሊየን ዶላር ገቢ ማግኘቱን ገለጸ

የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን በመጀመሪያዎቹ ስድስት ወራት 313 ነጥብ 6 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ገቢ ማግኘት መቻሉን አስታወቀ፡፡

ባለስልጣኑ 91ሺህ 812 ቶን ቡና ወደ ውጭ በመላክ 304 ሚሊየን 5 ዶላር የውጭ ምንዛሬ ማግኘቱን ገልጿል፡፡

ከቅመማ ቅመም 6 ነጥብ 7 ሚሊየን ዶላር እንዲሁም ከሻይ 1 ነጥብ 86 ሚሊየን በድምሩ 313 ነጥብ 6 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ገቢ ማግኘት መቻሉን የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር አዱኛ ደበላ ተናግረዋል፡፡

የስድስት ወር እቅድ አፈፃፀም ለግብርና አርብቶ አድርና አካባቢ ጥበቃ ቋሚ ኮሚቴ አቅርቦ ውይይት ተደርጎበታል፡፡

አርሶ አደሩን ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰሩ ያሉ አዳዲስ አሰራሮች ውጤት እንዳስገኙ የተገለፀ ሲሆን፣ በተለይም የባለ ልዩ ጣዕም ቡና ውድድር ውጤት ማስገኘት መቻሉ ነው የተነገረው፡፡

በቴክኖሎጂ የተደገፈ የቡና ልማት ክትትልና ድጋፍ ለማድረግ የሚያስችል ሶፍት ዌር በመዘጋጀት ላይ እንደሚገኝና ከጅማ ዩኒቨርሲቲና ከሚዛን ቴፒ ቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ኮሌጅ ጋር በመተባበር ሁለገብ የቡና እና ቅመማ ቅመም ስልጠና ሥርዓተ ትምህርት ተዘጋጅቶ ባለሙያዎችን ለማሰልጠን የስምምነት ሰነድ መፈረሙንም ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡

ብሔራዊ የቡና የንግድ ምልክት ወይንም ብራንዲግ በማዘጋጀት በተለያዩ አገራት የማስመዝገብ ሥራ እንደተጀመረም ጠቁመዋል፡፡

የቋሚ ኮሚቴው አባላት ባለስልጣኑ እየሰራ ያለው ስራ አበረታች እንደሆነ ጠቁመው አርሶ አደሩን ተጠቃሚ ለማድረግና ምርታማነትን ለማስፋፋት ትኩረት ተሰጥቶ መሰራት እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

(በሳራ ስዩም)