በስንዴ ምርታማነት የተመዘገበውን ውጤት በሌማት ትሩፋት ለመድገም ቁርጠኛ መሆናቸውን ክልሎች አስታወቁ

ኅዳር 22/2015 (ዋልታ) በአረንጓዴ አሻራና በስንዴ ምርታማነት የተመዘገበውን አመርቂ ውጤት በሌማት ትሩፋት ለመድገም ቁርጠኛ መሆናቸውን የአማራ፣ ኦሮሚያ እና አፋር ክልሎች አስታውቀዋል፡፡
የሌማት ትሩፋት የተሰኘ አገር አቀፍ መርኃ ግብር በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በይፋ መጀመሩ ይታወቃል፡፡
መርኃ ግብሩ አርሶ አደሩን፤ አርብቶ አደሩንና እና ሸማቹን የሚያገናኝ ድልድይ ከመሆኑ ባሻገር በቤተሰብ ብሎም በአገር ደረጃ በምግብ ራስን ለመቻል የምናደርገውን ጥረት እንደሚያፋጥን ታምኗል፡፡
ለቀጣዮቹ አራት አመታት የሚተገበረው፤ ይህ መርኃ ግብር ዋና ዓላማው የእንስሳት ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ እንደ ሀገር የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ ነው፡፡
በአረንጓዴ አሻራና በስንዴ ምርታማነት የተመዘገበውን አመርቂ ውጤት በሌማት ትሩፋት ለመድገም ቁርጠኛ መሆናቸውን ክልሎች አስታውቀዋል፡፡

ዋልታ ቴሌቪዥን ያነጋገራቸው የአማራ፤ ኦሮሚያ እና አፋር ክልል ግብርና ቢሮ አመራሮች በክልሎቻቸው የሚገኘውን መጠነ ሰፊ የእንስሳት ተዋጽኦ ሀብት ጥቅም ላይ ለማዋል እንደሚሰሩ ነው የገለፁት

እንደ ሀገር በአረንጓዴ አሻራና በስንዴ ልማት ላይ የተመዘገበውን ውጤት፤ በሌማት ትሩፋትም ህዝቡን በማሳተፍ በላቀ ውጤት ለማሳካት እንደሚሰሩ የገለፁት የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ኃላፊ ሀብተማርያም ከፍያለው (ዶ/ር) በእንስሳት ተዋጽኦ ላይ ትኩረት ተሰጥቶ የሚሰራ ከሆነ በኢትዮጵያ የምግብ ዋስትናን ሙሉ በሙሉ ለማረጋገጥ ትልቅ አቅም ይፈጥራል ነው ያሉት

የኦሮሚያ ክልል ግብርና ቢሮ ም/ኃላፊ ደበሌ ቶሌራ በበኩላቸው በቀጣዮቹ አምስት አመታት 300 ሺሕ የንብ ቀፎዎችን ለማሰራጨት እቅድ ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ከእንስሳት ተዋጽኦ ምርቶች ጋር ተያይዞ የምንከተለውን ባህላዊ የአመራረት አሰራር በዘመናዊ ለመተካት ጥረት እያደረግን ነው ያሉት ደግሞ የአፋር ክልል እንስሳት እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮ ኃላፊ ኢብራሂም መሀመድ ናቸው፡፡
በአገር አቀፍ ደረጃ የተጀመረው የሌማት ትሩፋት መርኃ ግብር የተሳካ እንዲሆን ቅንጅታዊ አሰራር ወሳኝ መሆኑም ተነስቷል፡፡

በሱራፌል መንግስቴ