ባለፉት 9 ወራት ከ2 ቢሊየን ብር በላይ በአስቸኳይ የሙስና መከላከል ስራ ማዳን መቻሉ ተገለጸ

ሚያዝያ 11/2016 (አዲስ ዋልታ) ባለፉት 9 ወራት 2 ቢሊየን 176 ሚሊየን 455 ሺሕ ብር በአስቸኳይ የሙስና መከላከል ስራ ማዳን መቻሉን የፌዴራል የሥነምግባር እና የፀረ-ሙስና ኮሚሽን አስታወቀ።

ሀገር አቀፍ የፀረ ሙስና ኮሚሽኖች የትስስር ጉባኤ ላይ የ2016 በጀት ዓመት ዘጠኝ ወራት የሥነምግባር ግንባታና የሙስና መከላለከል አገር አቀፍ አፈፃፀም ግምገማ በአዳማ ከተማ እየተካሄደ ይገኛል።

በመድረኩ ለክልሎች ከ354 ሺሕ በላይ ስልጠናዎች መሰጠቱ የተገለጸ ሲሆን ይህም ሙስናን በመከላከሉ ረገድ ትልቅ አስተዋጽኦ ማበርከቱ ተመላክቷል።

በ9 ወራት ውስጥ እንደ ሀገር 1 ሺሕ 451 የጥቆማ መረጃዎችን የመቀበል ስራ መስራቱን የገለጸው ኮሚሽኑ እንደ ሀገር 373 የአስቸኳይ ሙስና መከላከል ጥናት አጥንቶ ከ2 ቢሊዮን 176 ሚሊዮን 455 ሺሕ 388.7 ብር በላይ ማዳን መቻሉን አስታውቋል።

ከገንዘቡ በተጨማሪ መጠኑ 25 ሚሊየን በላይ የሆነ ካሬ ሜትር የሆነ የከተማና የገጠር ቦታ ከሙስና ምዝበራ ለማዳን ተችሏል ተብሏል።

ተቋሙ ከኢንሳ እና መሰል ተቋማት ጋር ቅንጅታዊ አሰራር በመዘርጋት ሙስናን የመከላከል ስራዎችን አጠናክሮ እየሰራ እንደሚገኝም ተመላክቷል።

በመድረኩ ላይ የፌደራልና የክልል የፀረ ሙስና ኮሚሸን ኮሚሽነሮችና ምክትል ኮሚሽነሮች ተገኝተዋል።

ማሕሌት መህዲ (ከአዳማ)