የአማራ ክልል ለ1 ሺሕ 460 ታራሚዎች ይቅርታ አደረገ

ብርሃኑ ጎሽም

ሚያዝያ 11/2016 (አዲስ ዋልታ) የአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ ለ1 ሺሕ 460 ታራሚዎች ይቅርታ ማድረጉን አስታወቀ፡፡

የቢሮው ኃላፊ ብርሃኑ ጎሽም በሰጡት መግለጫ የክልሉ መስተዳድር ምክር ቤት ሚያዝያ 7/2016 ዓ.ም ባካሄደው 6ኛ ዙር 3ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 6ኛ መደበኛ ስብሰባ ለሁለተኛ ዙር የሚሰጠውን ይቅርታ ምክንያት በማድረግ በክልሉ የይቅርታ አሰጣጥ ስርዓት መወሰኛ አዋጅ ቁጥር 136/1998 መሰረት ይቅርታ ማድረጉን ገልጸዋል።

ይቅርታ ከተደረገላቸው መካከል ሴቶች 29 መሆናቸውን የገለጹት ኃላፊው ይቅርታ የተደረገላቸው ታራሚዎች የፈጸሙት ወንጀል ይቅርታ የማይከለክል፣ ከተወሰነባቸው የጊዜ ቆይታ ውስጥ አንድ ሶስተኛ፣ አንድ አራተኛና አንድ አምስተኛውን የጨረሱ፣ ከከሳሾቻቸው ጋር እርቅ የፈጸሙ እንዲሁም እድሜያቸውን መሰረት ያደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ይቅርታ የተደረገላቸው ታራሚዎች ወደ ህብረተሰቡ ሲቀላቀሉ ለሌሎች አርዓያ ሆነው የተለመደ ማህበራዊ መስተጋብራቸውን ጤናማ በሆነ መንገድ ማስቀጠል እንዳለባቸው የተናገሩት ኃላፊው ህብረተሰቡም ይቅርታ ለተደረገላቸው ታራሚዎች አስፈላጊውን ድጋፍ ሁሉ እንዲያደርግላቸው ማሳሰቡን የክልሉ ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ መረጃ አመላክቷል፡፡