ብልፅግና ፓርቲ ከሌሎች ፓርቲዎች የሚለየው መደመርን እንደ መርህ በመያዙ ነው – የፓርቲው ፕሬዝዳንት ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

መጋቢት 2/2014 (ዋልታ) ብልፅግና ፓርቲ ከሌሎች ፓርቲዎች የሚለየው መደመርን እንደ መርህ በመያዙ ነው ሲሉ የብልፅግና ፓርቲ ፕሬዝዳንት ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

የብልጽግና ፓርቲ ፕሬዝዳንት ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የፓርቲውን የመጀመሪያ ጉባኤ አስመልክተው ባደረጉት ንግግር ብልጽግና ከሌሎች ፓርቲዎች የሚለየው መደመርን እንደ መንገድ፤ ብልጽግናን እንደ መዳረሻ የወሰደ እና በሀገር በቀል ሀሳብ ራሱን የተከለ በመሆኑ ነው ብለዋል፡፡

ብልጽግና በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በአፍሪካ ግዙፍ ፓርቲ መሆኑን ገልጸው 11 ሚሊዮን አባላት ያለው ፓርቲው በኢትዮጵያ ብልጽግናን ለማረጋገጥ ብቃት ያለው መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

ብልጽግና በብዙ ፈተናዎች ውስጥ ቢያልፍም የህዝብን የራስን ዕድል በራስ የማስተዳደር መብት በሪፌረንደም ማረጋገጥ የቻለ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ነውም ብለዋል፡፡

የፓርቲው የመጀመሪያ ጉባኤ ከፈተና ወደ ልዕልና የሚል ስያሜ የተሰጠው ድል ባለበት ሁሉ ፈተና ስላለ መሆኑንም ነው የጠቀሱት፡፡

በሳሙኤል ሓጎስ