ብልጽግና ድኅነትን ለመታገል የሚያደርገውን ጥረት እንደሚደግፉ የተለያዩ አገራት እህት ፓርቲ አመራሮች ተናገሩ

መጋቢት 2/2014 (ዋልታ) በብልፅግና ፓርቲ አንደኛ ጠቅላላ ጉባዔ ላይ የተገኙ የተለያዩ አገራት እህት ፓርቲ አመራሮች ገዢው ፓርቲ ብልጽግና ድኅነትን ለመታገል የሚያደርገውን ጥረት እንደሚደግፉና ከኢትዮጵያ ጎን እንደሚቆሙ ተናገሩ፡፡

በዚሁም በጉባዔው የተገኙት የቱርኩ ገዥ ፓርቲ (Akp) የውጭ ጉዳይ ዘርፍ ምክትል ሊቀመንበር ፌቭዚ ሳቨርዲ ኢትዮጵያና ቱርክ ለዘመናት የቆየ የጠነከረ ግንኙነት እናዳላቸው ገልጸው ኢትዮጵያ ለምትሰራቸው ማንኛውም ሥራዎች ከኢትዮጵያ ጎን እንደሚቆሙ ተናግረዋል፡፡

የኡጋንዳው ናሽናል ሙቭመንት ፓርቲ ምክትል ሊቀመንበር አልፐር ሲሞን ፒተር በርካታ ኢትዮጵያዊያን በኡጋንዳ እንደሚገኝ ጠቅሰው እኛ ኡጋንዳዊያን በተለይም የብልፅግና ፓርቲ ድኅነትን ለመታገል በሚያደርገው ጥረት አብረን እንሰራለን ብለዋል፡፡

ፓን አፍሪካኒዝምን ለማጠናከርና ዴሞክራሲን ለማሻሻል የሚሰራውን ሥራ ከኢትዮጵያ ጎን በመቆም አብረን እንሰራለን ያሉት ምክትል ሊቀመንበሩ ይህንን ለማሳካት እየሰራ ከሚገኘው ከብልፅግና ፓርቲ ጋር በጋራ እንሰራለንም ነው ያሉት፡፡

የጅቡቲው ፒፒል ራሊ ፎር ፕሮግረስ ፓርቲ ዋና ፀሐፊ ኤሊያስ ሙሳ ዳዋሌ የጅቡቲ መንግሥት የጠነከረች ኢትዮጵያ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለጅቡቲና ለአፍሪካ ታስፈልጋለች ብሎ እንደሚያምን ተናግረዋል፡፡
በሱራፌል መንግሥቴ