ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ነጻነቱንና ገለልተኝነቱን ጠብቆ ተልዕኮውን እንዲፈጽም በቁርጠኝነት እሰራለሁ – የቦርዱ ሰብሳቢ ሜላተወርቅ ኃይሉ

ሜላተወርቅ ኃይሉ

ታኅሣሥ 9/2016 (አዲስ ዋልታ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ነጻነቱንና ገለልተኝነቱን ጠብቆ ተልዕኮውን እንዲፈጽም በቁርጠኝነት ለመስራት መዘጋጀታቸውን የቦርዱ ሰብሳቢ ሆነው የተሾሙት ሜላተወርቅ ኃይሉ ገለጹ።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው 9ኛ መደበኛ ስብስባ ሜላተወርቅ ኃይሉን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ እንዲሆኑ ከመንግስት የቀረበለትን የውሳኔ ሀሳብ በአብላጫ ድምፅ አጽድቋል።

ቦርዱን ለመምራት በህዝብና በመንግስት የተሰጣቸውን የስራ ኃላፊነት በአግባቡ ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን የገለጹት ሰብሳቢዋ ቀደም ሲል የቦርዱን አፈጻጸም ለማሻሻል የተጀመሩ ስራዎች እንደነበሩ አስታውሰው 6ኛው አገራዊ ምርጫ በህዝብ ዘንድ ተዓማኒ ሆኖ መጠናቀቁ ለዚያ ማሳያ ነው ብለዋል።

ከዚህ ባለፈ በደቡብ ክልል የአደረጃጀት ህዝበ ውሳኔዎች በተሳካ ሁኔታ መከናወናቸው የተቋማዊ ለውጡ ውጤት መሆናቸውንም ነው የገለጹት።

የቦርዱን ስኬቶች በማስጠበቅ ነጻና ገለልተኛ ሆኖ እንዲቀጥልና በህዝብ ዘንድ ያለውን ተዓማኒነት ለመጨመር ከሌሎች አመራሮች ጋር በትጋት እንደሚሰሩ የተናገሩት ሰብሳቢዋ ቦርዱ የተለያዩ የማሻሻያ ስራዎችን እያከናወነ ቢሆንም የህዝብን ፍላጎት ከማርካት አኳያ የሚነሱ ክፍተቶችን መፍታትም ቀዳሚ ሥራቸው እንደሚሆን አመልክተዋል።

በቦርዱ አሰራር ላይ ቅሬታ ያለው ማንኛውም አካል በተዘጋጁ የጥቆማ መስጫዎች ጥቆማ እንዲሰጥም መጠየቃቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

የምክር ቤት አባላት በበኩላቸው አዲሷ ተሿሚ ከየትኛውም የፖለቲካ ወገንተኝነት ነጻ መሆናቸውን እንዲሁም ከትምህርት ዝግጅትና ከስራ ልምድ አኳያ ቦርዱን ለመምራት ብቁ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ሰብሳቢዋ ህዝብና መንግስት የጣለባቸውን ኃላፊነት በብቃትና በታማኝነት ሊወጡ እንደሚገባም ነው አባላቱ ያሳሰቡት።

አዲሷ የቦርዱ ሰብሳቢ ሜላተወርቅ ኃይሉ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሕግ የመጀመሪያ ዲግሪ፣ በሰላምና ደህንነት ጥናት ሁለተኛ ዲግሪ እንዲሁም በፐብሊክ አድሚንስትሬሽን የሁለተኛ ዲግሪያቸውን ከሀርቫርድ ዩኒቨርሲቲ አግኝተዋል።

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት በባለሙያነትና በአመራርነት ያገለገሉ ሲሆን ከየካቲት 2012 ዓ.ም እስከ የካቲት 2015 ዓ.ም ድረስ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የጽህፈት ቤት ኃላፊ በመሆን አገልግለዋል።