ብርሃን ባንክ ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ የ5 ሚሊዮን ብር ቦንድ ገዛ

መጋቢት 30 /2013 (ዋልታ) – ብርሃን ባንክ አክሲዮን ማኅበር ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ የሚውል የአምስት ሚሊዮን ብር ቦንድ በመግዛት ድጋፍ አድርጓል።

የባንኩ ፕሬዝዳንት አብርሃም አላሮ የግድቡ ግንባታ መጠናቀቁን የኢትዮጵያ ሕዝቦች በጉጉት የሚጠብቁበት ወሳኝ ምዕራፍ ላይ መድረሱን ተናግረዋል።

ግድቡ ሲጠናቀቅ በአገር ውስጥ ያለውን የኃይል እጥረት በከፍተኛ ሁኔታ ከማቃለል ባሻገር የውጭ ምንዛሬ በማስገኘት የላቀ ኢኮኖሚያዊ ሚና እንደሚጫወት ገልጸዋል።

የግድቡ የመሰረት ድንጋይ ከጣለበት ጊዜ ጀምሮ ባንኩ በድጋፍና በስጦታ የቦንድ ግዢ መፈፀሙንም አስታውሰው፤ ባንኩ በበርካታ አገራዊና ማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ በመሳተፍ የገንዘብ ድጋፍ ማድረጉን ገልጸዋል።

የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሕዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አረጋዊ በርሄ በበኩላቸው “ለግድቡ ግንባታ ድጋፍ ያደረጋችሁ በሙሉ አሻራችሁን እያስቀመጣችሁ ነው” ብለዋል።

ግድቡ የሉዓላዊነትና የአንድነት መገለጫ በመሆኑ ሕዝቡ ከግንባታው ጅማሬ አንስቶ እስከ አሁን ድረስ 15 ቢሊዮን 352 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ማድረጉንም ጠቅሰው፤ የቦንድ ግዥውና ስጦታው እንዲያጠናክርም አሳስበዋል።

ለሕዳሴው ግድብ ባለፉት 9 ወራት ከ1 ቢሊዮን 672 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ማሰባሰብ እንደተቻለም ገልፀዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።