የቱሉ ሞዬ ጂኦተርማል ፕሮጀክት የመጀመሪያው ጉድጓድ ቁፋሮ ተጠናቀቀ

መጋቢት 30/2013 (ዋልታ) – በሁለት ምዕራፍ ተከፍሎ እየተካሄደ የሚገኘው የቱሉ ሞዬ ጂኦተርማል ፕሮጀክት የመጀመሪያ የጉድጓድ ቁፋሮ መጠናቀቁ ተገለጸ።

ፕሮጀክቱ 150 ሜጋዋት ሃይል የሚያመነጭ ሲሆን ግንባታው በመካሄድ ላይ ይገኛል።

የቱሉ ሞዬ ጂኦተርማል ሃይል የቴክኒኒክ ሃላፊ ሲጉርጉር ጌሪሰን እንደገለጹት፤ የምስራቅ አፍሪካ የስምጥ ሸለቆ የሚያቋርጣት ኢትዮጵያ ከፍተኛ የሆነ የጂኦተርማል ኢነርጂ ዕምቅ ሃብት አላት።

በቱሉ ሞዬ ብቻ እስከ ሁለት ሺህ ሜጋዋት ሃይል በጂኦተርማል ማመንጨት እንደሚቻል መጠቆማቸውን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል ገልጿል።

በሁለት ምዕራፍ የሚካሄደው የቱሉ ሞዬ ፕሮጀክት 10 ጉድጓዶች እንደሚኖሩት የገለጹት የቴክኒክ ሃላፊው፤ የጉድጓድ ቁፋሮ ስራው እየተካሄደ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

የቱሉ ሞዬ ጂኦተርማል ፕሮጀክት ሳይት ሃላፊ ሩፋት ማይና በበኩላቸው የመጀመሪያው የጉድጓድ ቁፋሮ ተጠናቆ ሁለተኛው መጀመሩን ይፋ አድርገዋል።

መቆፈር ካለበት 2 ሺህ 500 ሜትር ውስጥ ከአንድ ሺህ ሜትር በላይ መቆፈሩንም ጠቁመዋል።

ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ የኤሌክትሪክ ሃይል ከማመንጨት ባለፈ ሰፊ የስራ እድል የሚፈጥር እንደሆነ ተነግሯል።

ከኢዜአ የተገኘው መረጃ እንዳመላከተው የቱሉ ሞዬ ፕሮጀክት በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ ይጠናቀቃል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን 800 ሚሊዮን ዶላር ያህል ወጪ ይጠይቃል።