ብቁ እና ተወዳዳሪ የሆኑ ባለሙያዎችን ለማፍራት ምቹ የሆነ መሰረተ ልማት እንደሚያስፈልግ ተገለጸ

ግንቦት 30/2013 (ዋልታ) – ብቁ እና ተወዳዳሪ የሆኑ ባለሙያዎችን ለማፍራት ምቹ የሆነ መሰረተ ልማት እንደሚያስፈልግ ተገለጸ፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ አቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ከ77 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ የተደረገባቸው የልማት ፕሮጀክቶች በዛሬው ዕለት ተመርቀዋል።

በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የተገኙት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአገልግሎት ሰጭ ተቋማት አስተባባሪ አቶ ጃንጥራር አባይ ብቁ እና ተወዳዳሪ የሆኑ ባለሙያዎችን ለማፍራት ምቹ የሆነ መሰረተ ልማት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡

በዚህም መሰል መሰረተ ልማቶችን በመገንባት ብቁ ዜጋ ለማፍራት ሁሉም ኃላፊነቱን ሊወጣ እንደሚገባ ተናግረዋል።

ዛሬ ከተመረቁ ፕሮጀክቶች መካከል የአቃቂ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ባለ ሰባት ፎቅ ህንፃ እና የጥሩነሽ ቤጂንግ ሆስፒታል ማስፋፊያ ግንባታዎች ይገኙበታል።

አዲስ አበባን የብልፅግና ተምሳሌት ለማድረግ በተያዘው እቅድ ከ1 ሺህ በላይ ፕሮጀክቶች ተሰርተው እየተመረቁ ሲሆን፣ ለማህበረሰቡ ከፍተኛ የሆነ አገልግሎት ከሚሰጡ የማስፋፊያ ግንባታ ፕሮጀክቶች መካከል አንዱ የጥሩነሽ ቤጂንግ ሆስፒታል መሆኑ ተገልጿል።

በሆስፒታሉ እየጨመረ የመጣውን የታካሚ ቁጥር ከግምት ውስጥ በማስገባት ማስፋፊያ መደረጉ በምረቃ ሥነሥርአቱ ላይ የተገለፀ ሲሆን፣ አዲስ አበባን ለጤና ቱሪዝም ምቹ እንድትሆን መንገድ ይከፍታልም ተብሏል።

ሌላው ለምረቃ የበቃው ከ30 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ የተደረገበት የግብዓት ማከማቻ መጋዘን ሲሆን፣ ከዚህ ቀደም ከተለያዩ የተራድኦ ድርጅቶች የሚገኙ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚኖሩ የማህበረሰብ ክፍሎች አገልግሎት የሚውሉ ቁሳቁስ ለማስቀመጥ ችግር እንደነበረ ተገልጿል።

በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ አስተዳደር የተገነባው የግብዓት ማከማቻ መጋዘን በክፍለ ከተማው የነበረውን ችግር ይፈታል ተብሏል።

በከተማ አስተዳደሩ ከሚገኙት 17 የቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ተቋማት ውስጥ አንዱ የሆነው የአቃቂ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ የማስፋፊያ ግንባታ በማካሄድ ባለ 7 ፎቅ ህንፃ አስገንብቶ አስመርቋል።

የአቃቂ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ዲን አቶ ደመላሽ ተስፋዬ የአዲስ ህንፃ ግንባታ ኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚን ለማሳደግ ለዘርፉ የሰጠችውን ትኩረት የሚያሳይ መሆኑን ገልጸው፣ ኮሌጆች ወጣቱን የህብረተሰብ ክፍል አሰልጥኖ ወደ ስራ በማሰማራቱ ረገድ ጉልህ ሚና እንዳላቸው ጠቁመዋል።

(በቁምነገር አህመድ)