በቀዳማዊት እመቤት ጽሕፈት ቤት የተገነቡ 8 ት/ቤቶች ለርክክብ ዝግጁ ሆኑ

በቀዳማዊት እመቤት ጽሕፈት ቤት የተገነቡ ተጨማሪ ስምንት ትምህርት ቤቶች ለርክክብና ለአገልግሎት ዝግጁ መሆናቸውን ጽሕፈት ቤቱ አስታወቀ።

የጽ/ቤቱ ዳይሬክተር አቶ ሙሉቀን ፋንታው እንደገለጹት፤ ጽሕፈት ቤት የሚያስገነባቸው የትምህርት ተቋማት ፕሮጀክቶች በአብዛኛው በመጠናቀቅ ላይ ናቸው።

ግንባታቸው ተጠናቆ ርክክብ የሚፈጸምባቸው ትምህርት ቤቶች በአፋር ክልል ዱብቲ፣ በጋምቤላ አኝዋሃ ዞን፣ በቤኒሻንጉል ክልል አሶሳ እና መተከል ዞን ፣ በሶማሌ ክልል ጅግጅጋ ዞን ፤ በዲላ ከተማ 02 እና 06 ቀበሌዎች፣ በአማራ ክልል ሰሜን ጎንደር ደባርቅ ከተማ እና ዋግኸምራ ዞን ሳህላ ሰለምት ወረዳ የተገነቡ መሆናቸውን ገልፀዉ ጽህፈት ቤቱ ከ760 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪም አድርጓል ብለዋል፡፡

ግንባታቸው ቀድመው የተጠናቀቁና ርክክባቸው ተፈጽሞ ስራ የጀመሩት አምስት ትምህርት ቤቶች መኖራቸውን ያስታወሱት ዳይሬክተሩ፤ በአማራ ክልል ጎንደር ሎዛ ቀበሌ፣ ደቡብ ወሎ ጦሳ ሰላማ ቀበሌ፣ በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ ዞን ሊበን ጭቋላ ቀበሌ፣ ምዕራብ ጉጂ ዞን እና ሰሜን ሸዋ ዞን ውጫሌ ወረዳ ጃክ ቀበሌ የሚገኙት መሆናቸውንና አሁን ላይ ተማሪዎችን ተቀብለው በማስተናገድ ላይ እንደሆኑ ገልጸዋል።

(ምንጭ፡- ኢፕድ)