ቦርዱ በ6ኛው አጠቃላይ ምርጫ ሂደት ላይ በተደረገ የግምገማ ውጤት ዙሪያ እየተወያየ ነው

ሚያዝያ 20/2014 (ዋልታ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ስድስተኛው አጠቃላይ የምርጫ ሂደት ላይ በተደረገ የግምገማ ውጤት ላይ ውይይት እያካሄደ ነው።
የውይይት መድረኩ ስድስተኛው አጠቃላይ የምርጫ ሂደት ላይ የተደረገ የግምገማ ውጤት እንዲሁም የተገኙ ውጤቶች ማስተዋወቂያና ማጠናቀቂያ ሁነት መሆኑ ተገልጿል።
በመማማር ሂደት ላይ የተገኙ ትምህርቶችን፣ የምርጫ ቦርድ ተግዳሮቶችንና ውጤታማ ተሞክሮዎችን ለባለድርሻ አካላት ተንትኖ ለማቅርብ እንዲሁም ምክረ ሀሳቦችን ለማጠናከርም እንደሆነ ተነግሯል።
የቦርዱ ሰብሳቢ ብርቱካን ሚዴቅሳ በመድረኩ መክፈቻ ላይ ባደረጉት ንግግር የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ስድስተኛው አጠቃላይ ምርጫ ተከትሎ ካከናወናቸው የተለያዩ ተግባራት የተገኙ ትምህርቶችን የመሰነድ ተግባር ማከናወኑን ገልጸዋል።
ቦርዱ በምርጫ ላይ ከተሳተፉ ባለድርሻ አካላት አስተያየት በመሰብሰብ ግብዓትን አጠናክሮ በቀጣይ ለሚያከናውናቸው ምርጫዎችም ሆነ አጠቃላይ ተግባራት እንደ ግብዓት የሚጠቀምበት መሆኑም ጠቁመዋል።
መድረኩ የተገኙ ስኬቶችን ለማስቀጠል ስህትቶችን ለይቶ በማውጣት ለሚቀጥለው ምርጫ እንዳይደገሙ ምክረ ሀሳቦችን ለመውሰድ ያለመም እንደሆነም ጠቅሰዋል።
አውደ ጥናቱ ዛሬን ጨምሮ ለሁለት ተከታታይ ቀናት የሚካሄድ ሲሆን የመማማርና የግምገማ ሂደት ቅኝት፣ ተቋማዊ የሪፎርም ሥራና የምርጫ እቅድ፣ የምርጫ አካሄድ የሚሉና ሌሎች መሰል ርዕሰ ጉዳዮች የመድረኩ አጀንዳዎች እንደሆኑ ኢፕድ ዘግቧል።
በመድረኩ ላይ አጋር ድርጅቶች፣ የሲቪል ማኅበረሰብ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ጨምሮ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ተወካዮች ታድመዋል።