ተመድ በኢትዮጵያ ለሰብአዊ ድጋፍ የሚውል ከ35 ሚሊየን ዶላር በላይ ድጋፍ አደረገ

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአስቸኳይ ጊዜ ፈንድ በኢትዮጵያ ለሰብአዊ ድጋፍ የሚውል ከ35 ሚሊየን ዶላር በላይ ድጋፍ ማድረጉን አስታወቀ።

የፌደራል መንግስት በትግራይ ክልል ህግ በማስከበር ሂደት ጉዳት ለደረሰባቸው ሰዎች የሰብአዊ ድጋፍ ለማቅረብ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት 35 ነጥብ 6 ሚሊየን ዶላር ድጋፍ መልቀቁን አስታውቋል።

የገንዘብ ድጋፉ በተለይ በትግራይ ክልል አስቸኳይ የሰብአዊ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ዜጎች የሚሰጥ መሆኑ ተገልጿል።

ድጋፉ ለንፁህ መጠጥ ውሃ፣ የንጽህና መጠበቂያና የህክምና ቁሳቁስ አቅርቦት ይውላል ተብሏል።

በኢትዮጵያ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአስቸኳይ ጊዜ ፈንድ ለዜጎች የህክምና አገልግሎት እንዲያገኙ ጓንት፣ መድሃኒትና ሌሎች የህክምና ቁሳቁስ እንዲሟሉ አግዛለሁ ብሏል።

ከትግራይ ክልል ወደ ሱዳን ለተሰደዱ ኢትዮጵያውያን መጠለያ፣ የመጠጥ ውሃና የጤና አጠባበቅን ጨምሮ የህይወት አድን ድጋፎች ቅድሚያ ይሰጣቸዋልም ተብሏል።

በድጋፉ ሴቶች፣ ህጻናት፣ አዛውንቶችና አካል ጉዳተኞች ቅድሚያ እንደሚሰጣቸው ተገልጿል።

የተባበሩት መንግስታት ማዕከላዊ የአስቸኳይ ጊዜ ምላሽ ፈንድ በ2020 በ52 አገሮች ለ65 ሚሊየን ሰዎች የህይወት አድን ድጋፍና ሌሎች እርዳታዎችን ማድረጉን አስታውቋል።

ይህም ወደ 900 ሚሊየን ዶላር ግምት እንዳለው መነገሩን ኢዜአ ዘግቧል።