የአዲግራት እና ውቅሮ ከተሞች ዳግም የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተጠቃሚ ሆኑ

በትግራይ ክልል ተከስቶ በነበረው የፀጥታ ችግር የወደሙ የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማቶችን በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት እና በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል ቅንጅት በተሰራ ስራ በአዲግራትና ውቅሮ ከተሞች ተቋርጦ የነበረው የኤሌክትሪክ አገልግሎት ከታህሳስ 08 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ ዳግም ተመልሷል፡፡

የትግራይ ክልል ኤሌክትሪክ አገልግሎት የቴክኒክ ባለሞያዎች ጉዳት የደረሰባቸውን የዝቅተኛና መካከለኛ ኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ መስመር ላይ ባደረጉት የጥገናና መልሶ ግንባታ ስራ እንዲሁም የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል የቴክኒክ ባለሞያዎች በከፍተኛ ኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ መስመር ላይ ባደረጉት የጥገናና መልሶ ግንባታ ስራ በሁለቱ ከተሞች ተቋርጦ የነበረው የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ዳግም አገልግሎት መስጠት ጀምሯል፡፡

በአክሱም፣ በሽሬና አድዋ ከተሞች የተቋረጠው የኤሌክትሪክ አገልግሎት ዳግም እንዲመለስ ሁለቱ ተቋማት በቅንጅት እየሰሩ ይገኛሉ።

በክልሉ በተከሰተው የፀጥታ ችግር የወደሙ የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማቶች በአፋጣኝ ወደ አገልግሎት ለመመለስ ሲሰራ መቆየቱ የሚታወስ ነው ሲል የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አስታውቋል፡፡