ሰኔ 04/2013 (ዋልታ) – በምስራቅ ሸዋ ዞን ተሽከርካሪ የዘረፉ 12 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተደረገባቸው መሆኑን ፖሊስ አስታውቋል።
በዞኑ ፖሊስ መምሪያ የሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን ኃላፊ ኮማንደር አስቻለው ዓለሙ እንደገለፁት በዞኑ በአዳሚ ቱሉ ጅዱ ኮምቦልቻና ሊበን ወረዳዎች የተሽከርካሪ ዘረፋ ወንጀል የፈጸሙ 12 ግለቦች በቁጥጥር ስር ውለዋል።
ግለሰቦቹ ንብረትነቱ የሰላም ውሃ ማምረቻ ፋብሪካ የሆኑ አንድ ኤፍ ኤስ አር እና አንድ አይሱዙ እንዲሁም አንድ ሲኖ ትራክ በድምሩ ሶስት ተሽከርካሪዎችን ሚያዝያ 14 ቀን 2013 ዓ.ም ጨለማን ተገን በማድረግ መዝረፋቸውን ገልጸዋል።
ዘራፊዎቹ የሀሰት ሰሌዳ ቁጥር በተለጠፈባቸው ሁለት ቪትስ ተሽከርካሪዎችና በጦር መሳሪያ በመታገዝ የተሽከርካሪ ዝርፊያውን መፈጸማቸውን ተናግረዋል።
በተለይም የኤፍ ኤስ አር አሽከርካሪውን ዛፍ ላይ አስረው የዘረፏቸውን ተሽከርካሪዎች ይዘው መሰወራቸውን ኮማንደር አስቻለው ተናግረዋል፡፡
የዞኑ ፖሊስ መምሪያም ባደረገው ክትትል ተጠርጣሪ ዘራፊዎቹ የዘረፋ ወንጀሉን ለመፈጸም ሲጠቀሙባቸው ከነበሩ ተሽከርካሪዎች ጋር በቁጥጥር ስር አውሎ ምርመራ እየተካሄደባቸው መሆኑን መግለፃቸውን ኢዜአ ዘግቧል።