ተፈናቃይ ተማሪዎችን ለማስተማር ጥረት እየተደረገ መሆኑ ተገለጸ

ጥቅምት 4/2014 (ዋልታ) በአማራ ክልል ተፈናቃይ ተማሪዎችን በሁሉም የክልሉ ዞኖች ለማስተማር ጥረት እየተደረገ መሆኑን የክልሉ ትምህርት ቢሮ አስታወቀ።

የትምህርት ቢሮው ምክትል ኃላፊ ሙላው አበበ ለኢፕድ እንደገለጹት የ2014 ዓ.ም የትምህርት ዘመን ከመጀመሩ አስቀድሞ የተለያዩ የዝግጅት ስራዎች ሲከናወኑ ቆይተዋል።

በክልሉ ከየአካባቢው ተጨባጭ ሁኔታ ጋር በማጣጣም ከተወሰኑ ዞኖች፣ ማለትም ደሴ ከተማ አስተዳደር፣ ሰሜን ጎንደርና እብናት አካባቢዎች በስተቀር መስከረም 24 በሁሉም ዞኖችና ከተማ አስተዳደሮች ትምህርት መጀመሩን ተናግረዋል።

የምስራቅ ጎጃም አስተዳደርና የትምህርት አመራር በትህነግ ቡድን ምክንያት ከቤት ንብረታቸውና ከአካባቢያቸው ተፈናቅለው ወደ ዞኑ የሚመጡ ተፈናቃዮችን ተቀብሎ ለማስተማርና ድጋፍ ለማድረግ በወሰደው አቅጣጫ ተማሪዎችን በግል ትምህርት ቤቶች ሳይቀር ተቀብሎ ለማስተማር ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛል ብለዋል።

የተፈናቃይ ተማሪዎችን በተመለከተ የክልሉ መንግሥትና ትምህርት ቢሮው ባስቀመጠው አቅጣጫ በሁለት መንገድ እየተስተናገዱ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

አክለውም ተፈናቃይ ተማሪዎች ለመማር ፈልገው ሲመጡ ማንኛውም ትምህርት ቤት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲያስተናግድ ማድረግ የመጀመሪያው ስልት ነው ብለዋል።