ትዴፓ አሸባሪው ትሕነግ የትግራይ ሕዝብ እርዳታ እንዳያገኝ እያደረገ ነው አለ

ጥር 17/2014 (ዋልታ) አሸባሪው ትሕነግ የሰብኣዊ ድጋፍ መተላለፊያ መስመሮችን የጦርነት ቀጣና በማድረግ የትግራይ ሕዝብ እርዳታ እንዳያገኝ እያደረገ መሆኑን የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ትዴፓ) አስታወቀ።

የትግራይ ሕዝብ አሁን ላይ በአሸባሪው ቡድን በቃላት መግለጽ በማይቻል አስከፊ ጭቆና ሥር እንደሚገኝም ነው ፓርቲው የገለጸው።

ትዴፓ በሰጠው መግለጫ የፓርቲው ዋና ጸሐፊ ጊደና መድኅን “አሸባሪው ሕወሓት የትግራይ ሕዝብ ባለፉት 47 ዓመታት እጅግ ፈታኝ ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊና ቁሳዊ ችግሮች እንዲገጥሙት በማድረግ ረገድ ዋነኛ ተጠያቂ ነው” ብለዋል።

እንደኢዜአ ዘገባ ኢትዮጵያን ወዳልተፈለገ ጦርነት እንድትገባ በማድረግም ከትግራይ ሕዝብ በተጨማሪ የአማራና አፋር ክልል ሕዝቦች ላይ ጉዳት ማድረሱንም ገልጸዋል።

ፓርቲው መላ ኢትዮጵያዊያን የትግራይን ሕዝብ ከትሕነግ የጭቆና ቀንበር ነፃ ለማውጣት በሚያደርገው ፖለቲካዊ ትግል የበኩላቸውን ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርቧል።