የሰብኣዊ መብቶች ም/ቤት ውሳኔ በኢትዮጵያ ምድር እንደማይፈፀም መንግሥት አስታወቀ

ታኅሣሥ 12/2014 (ዋልታ) – የተባበሩት መንግሥታት የሰብኣዊ መብቶች ምክር ቤት የፖለቲካ አጀንዳን ይዞ ያሳለፈው ውሳኔ በኢትዮጵያ ምድር እንደማይፈፀም መንግሥት አስታወቀ፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን መቀመጫቸውን አዲስ አበባ ላደረጉ የአውሮፓ፣ አሜሪካ፣ ኢስያ እና መካከለኛው ምስራቅ አገራት ከአምባሳደሮችና ዲፕሎማቶች በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
አምባሳደር ሬድዋን የፖለቲካ ፍላጎት ባላቸው አካላት ገፋፊነት እና አስተባባሪነት የተባበሩት መንግሥታት የሰብኣዊ መብት ምክር ቤት ያሳለፈውን ውሳኔ ኢትዮጵያ እንደማትቀበል ተናግረዋል። ውሳኔው በኢትዮጵያ ምድር ተፈፃሚ እንደማይሆን አብራርተዋል።
ምክር ቤቱ የሽብር ቡድኑ በወረራ በቆየባቸው የአማራ እና አፋር አካባቢዎች የፈጸማቸውን መጠነ ሰፊ ሰብአዊ እና ቁሳዊ ጥፋት በማውገዝ ምርመራ እንዲካሄድ ውሳኔ ቢያሰተላልፍ ኖሮ ተገቢና የሚያስመሰግነው እንደነበርም ገልጸዋል።
የሕወሓት ሽብር ቡድን የእርዳታ አቅርቦትን ለማስተጓጎል የሚወስደው የእብሪት ተግባርን የዓለም ዐቀፉ ማኅበረሰብ በቸልታ መመልከቱን ጠቅሰው፤ በመንግሥት በኩል ግን የሰብኣዊ እርዳታ ተደራሽነትን ለማረጋገጥ የሚቻለውን ሁሉ ማድረጉን አመልክተዋል።